በተንቀሳቃሽ ስልክ በተደጋጋሚ የሚላኩ አጭር የጽሁፍ መልዕክቶች የህብረተሰቡን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ እያወኩ ነው

4005

አዲስ አበባ ሚያዚያ 26/2010 ከተጠቃሚው ፍላጎት ውጪ በተንቀሳቃሽ ስልክ በተደጋጋሚ የሚላኩ አጭር የጽሁፍ መልዕክቶች የህብረተሰቡን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ እያወኩ መሆኑ ተገለጸ።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ሰዎች እንደተናገሩት፤ የማይታወቁ፣ ጠቀሜታቸው እምብዛም ያልሆነና የተሳሳተ መረጃ ያላቸው መልእክቶች በግል ተንቀሳቃሽ ስልካቸው በተደጋጋሚ እየገባ እየረበሻቸው ነው።

ያለፈቃዳቸው የሚገቡ መልዕክቶችንም ለማስቀረት የተዘረጋው አሰራር ውጤታማ ባለመሆኑ ለአላስፈላጊ ወጪ እየዳረጋቸው መሆኑን ነው የሚናገሩት።

‘’የሚላኩ መልዕክቶች አብዛኞቹ አስተማሪዎች አይደሉም እኛ ወጣቶች በአሁኑ ወቅት የምንማርበትና ትክክለኛ የሆነ መረጃ የሚሰጠን እንፈልጋለን’’ያሉን ወጣት ሄርሜላ ጳውሎስና የአብስራ አብዱራህማን ናቸው።

ነገር ግን በየሰዓቱ የሚላኩ መልዕክቶች በመብዛታቸው የራሳቸውን ትክክለኛ መልዕክት እንዳያነቡ እያደረጉና አብዛኞቹም ፋይዳ ቢስ በመሆናቸው መሰላቸታቸውን ተናግረዋል።

መልዕክቶቹን ለማጥፋት ከኢትዮ-ቴሌኮም መረጃ ወስደው ቢጠቀሙም መልዕክቱን እንዲቀር ማድረግ አለመቻላቸውን ጠቁመዋል።

ወጣት ዮሴፍ ወልደስላሴና ወይዘሮ መሰለች ገብረጻዲቅ በበኩላቸው ከመልዕክቶቹ ውስጥ አገራዊ ፋይዳ ያላቸው ጥቂቶቹ በመሆናቸው እነሱን እንቀበላለን።

የሚላኩት መልዕክቶች ከደንበኛው ፍላጎት ውጪ የሆነና የማይመለከተው እንደሆነ በመግለጽ ወደግል ስልካቸው መልዕክቱ እንዳይመጣ ፍላጎት አላቸው።

ይህ ደግሞ የአንድን ግለሰብ የግል ሁኔታን የሚጋፋ በመሆኑ መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።

የኢትዮ ቴሌኮም ኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ኦፊሰር አቶ አብዱራሂም አህመድን ለኢዜአ እንዳሉት በቴሌኮሙ ከ417 በላይ ድርጅቶች አጭር የጽሁፍ መልዕክት እንዲያስተላልፉ በአለም ዓቀፍ ደረጃ ባለው አሰራር መሰረት ውል ገብተዋል።

ከገቡት ውስጥ ህጉን ተከትለው የማይሰሩ እንዳሉ በህብረተሰቡ ጥቆማና ቴሌኮሙ በሚያደርገው ማጣራት ተደርሶባቸዋል።

በዚህም በቅርቡ ከ60 በላይ ድርጅቶች ከ50ሺህ ብር ቅጣት ጀምሮ አገልግልት እስከማቋረጥ የሚደርስ እርምጃ ተወስዶባቸዋል፤ ነገር ግን አሁንም ይህንን ተግባር የሚፈጸሙትን በጋራ ለመከላከል ህብረተሰቡ በ994 በማስመዝገብ ማስቀጣት ይገባዋል።

የሚያስጠይቀው ከሰዓት ገደብ ውጪ መላክ ደንበኛው ሳይፈልግ መላክ፣ ደንበኛው ካለው ውጪ መላክና ሌሎችም ከአስር በላይ ጉዳዮች አሉ።

ይህ አገልግሎት በእኛ አገር የመጀመሪያው እንደመሆኑ መጠን ብዙ ችግሮች እየተሰተዋሉበት ነው ይህም በሂደት እየጠራ የሚሄድ መሆኑን አቶ አብዱረሂም ተናግረዋል።

ኢትዮ-ቴሌኮም ከሚያውቃቸውና ውል ከገቡት ውጪ በኢንተርኔት የሚለቀቁ አንዳንድ መልዕክቶች እንዳሉ የሚታወቅ እንደሆነም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የ3ጂ የቴሌኮም የሞባይል አገልግሎት ተጠቃሚ ቁጥር ከ85 በመቶ በላይ መድረሱን ከቴሌኮሙ የተገኘው መረጃ ያሳያል።