በትግራይ በክረምት ወቅት 48ሺህ ሄክታር መሬት የሚሸፍኑ ችግኞች ይተከላሉ

74

ግንቦት 23/2011 በትግራይ በክረምቱ ወቅት 48ሺህ ሄክታር መሬት የሚሸፍኑ ችግኞች እንደሚተከሉ የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ ገለጸ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊና የተፈጥሮ ሀብትና ምግብ ዋስትና አስተባባሪ አቶ ክፍሎም አባዲ ለኢዜአ እንዳስታወቁት በክረምቱ ወቅት 78 ሚሊዮን ችግኞች ለተከላ ተዘጋጅተዋል።

አርሶ አደሮችም ከግብርና ሥራቸው በተጓዳኝ ለተከላው መዘጋጀታቸው ተናግረዋል።

የክልሉ መንግሥት 65 በመቶ የሚሸፍነው ተራራማና ተዳፋት መሬት በደን ለማልማት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም የገለጹት ምክትል ኃላፊው፣በአሁኑ ወቅት ለተከላ የሚሆኑ ጉድጓዶች ቁፋሮ እየተካሄደ ነው ብለዋል።

በየወረዳው የሚተከሉት ችግኞች እንክብካቤና ክትትል እንዲደረግላቸውም የደን ክልልነቱን የሚያመለክት   ካርታ መዘጋጀቱንም አስታውቀዋል።

ኅብረተሰቡ በድህረ ተከላ ወቅት ውሃ የማጠጣት፣ ፍግ የመጨመርና እርጥበት  ማቆየት ተግባራት እያከናወነ መሆኑን አቶ ክፍሎም ተናግረዋል።

በዚህም በየዓመቱ ለኃይል፣ለግንባታና ለእንስሳት መኖ እንዲውሉ ከሚተከሉ ችግኞች 73 በመቶ እየጸደቁ ናቸው ብለዋል።

የክልሉ ሕዝብ በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ባከናወነው ሥራ ከ30 ዓመታት በፊት ሦስት በመቶ የነበረው የደን ሽፋን አሁን ወደ 15 በመቶ  ማደጉንም ገልጸዋል።

በትግራይ ደቡባዊ ዞን በእምባአላጀ ወረዳ አርሶ አደር ግርማይ አብርሃ በበኩላቸው በየዓመቱ እስከ 100 የሚሆኑ የዛፍ ችግኞች በማሳቸው ዙሪያ እንደሚተክሉ ተናግረዋል።

ከማይጨው የችፑድ ፋብሪካ ባላቸው የገበያ ትስስርም የደረሱ ባህር ዛፎች በማቅረብ በዓመት እስከ 10 ሺህ ብር ገቢ እያገኙ መሆናቸወን ገልጸው፣ዘንድሮም ተከላ ለማከናወን ቦታ በማዘጋጀት ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

ለችግኝ ተከላ የሚሆኑ ቦታዎች አስቀድሞ ማዘጋጀትና ቀጣይነት ያለው እንክብካቤ ማድረግ ችግኞች የመጽደቅና የማደግ ዕድላቸውን እንደሚያሰፋው የተናገሩት ደግሞ በእንደርታ ወረዳ የፈለገ ሕይወት ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አሰፋ ግርማይ ናቸው።

ከየካቲት ወር ጀምሮም ለተከላ የሚሆን ቦታ በመለየትና ከእንስሳት ንክኪ ነፃ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም