በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች መምህራን ሰልፈ እያካሄዱ ነው

112

ግንቦት 23/2011 በአማራ ክልል በተለያዩ ከተሞች የአካዳሚክ ነጻነትና ጥቅሞቻችን ይከበሩ በሚል መምህራን ሰላማዊ ሰልፍ እያካሄዱ ነው፡፡

መምህራኑ ዛሬ በባህር ዳር፣ ጎንደር፣ ደሴ፣ ወልዲያ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ደብረ ብርሃንና ሌሎች ከተሞች እያካሄዱ ባለው ሰልፍ ችግሮቻቸው እንዲፈቱላቸው መንግስትን ጠይቀዋል።

በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ባለው ሰልፍ መምህራኑ “የሁለት ዓመት የጎንዮሽ ጭማሬ ውይም እርከን መከልክል የለበትም፤ ተመሳሳይ የትምህርት ዝግጅት ያላቸው መምህራን የደመወዝ አከፋፈል ልዩነት መኖር የለበትም፤ የትምህርት ባለሙያዎች የትምህርት የደረጃ እድገት አለመኖር ለትምህርት ጥራት እንቅፋት ሁኗል” የሚሉ መፈክሮችን አስምተዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የመምህራን የአካዳሚክ ነጻነት ይከበር፤ ለመምህራን የደመወዝና የጥቅማጥቅም ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ይሰጥ፤ የመምህራን የቤት መስሪያ ቦታ አሰጣጥ ደንብ 150/2009 በተገቢው መንገድ ይከበርልን፤ ግድያና ማፈናቀል ይቁም የሚሉና መሰል መፈክሮችን አሰምተዋል።

ሰልፈኞቹ በተጨማሪ የክልሉ የመምህራን ስልጠና አሰጣጥ ወጥ እንዲሆንና ስልጠና ሳይወስዱ መምህር መሆን እንደማይቻል በመግለጽ የሙያውን ክብር የሚያጎድፉ ተግባራትን እንደሚቃወሙ አስታውቀዋል።

 “የመልካም አስተዳደር ችግሮች ይፈቱ፤ የትምህርት ተቋማት ከሃይማኖትና ከፖለቲካ ነጻ ይሁኑ” የሚሉትም በመምህራኑ ከተስታገቡ መፈክሮች መካከል ይገኙበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም