በከተማዋ በቂ የግብይት ማዕከላት ባለመኖሩ አትክልትና ፍራፍሬን በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት አልቻልንም ...ተጠቃሚዎችና ነጋዴዎች

197

ግንቦት 23/2011 በአዲስ አበባ ከተማ በቂ የአትክልት እና ፍራፍሬ የግብይት ማዕከላት ባለመኖሩ  ምርቶቹን በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት አለመቻላቸውን ነጋዴዎች እና ተጠቃሚዎች ተናገሩ፡፡

የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ነዋሪዋ  ወይዘሮ ነፃነት አለማየሁ እንዳሉት በአከባቢያቸው የአትክልት እና ፍራፍሬ የግብይት ማዕከል ባለመኖሩ በአብዛኛው ከሱቅ እና መንገድ ላይ ከሚያዞሩ  ነጋዴዎች መግዛት ግድ ሆኖባቸዋል።

የአካባቢያቸው  አትክልት እና ፍራፍሬ መሸጫ ዋጋም “ከፒያሳ አትክልት ተራ” የተጋነነ መሆኑን  የተናገሩት ወይዘሮ ነፃነት፤  ከዋጋው  በላይ  ምርቶቹ ጥራታቸው የተጠበቀ አለመሆኑን ነው የጠቀሱት፡፡

ህብረተሰቡ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን  በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያገኝበት የገበያ ማእከላት በየቦታው መገንባት እንዳለበትም ጨምረው ተናግረዋል።

በአትክልት እና ፍራፍሬ  ችርቻሮ ንግድ የተሰማራው ወጣት ዳኘው ማስረሻ በበኩሉ    የግብይት ሰንሰለት መረዘም ምርቱን በተመጣጣኝ ዋጋ ለተጠቃሚ እንዳያቀርቡ ማድረጉን  ገልጸዋል፡፡

ምርቶቹን ከፒያሳ አትክልት ተራ እያመጣ የሚሸጥ በመሆኑ፤ የትራንስፖርት  እና የሰራተኞች ክፍያ ወጪ ስለሚያስብበት  በውድ ዋጋ ለመሸጥ እንደሚገደድም ተናግሯል።

ከአምራቹ እስከ ተጠቃሚው  የግብይት ሰንሰለት  የተወሳሰበ ነው ያለው ወጣት ዳኘው፤ ምርቱን በቀጥታ ከምራቾች በመረከብ የምንሸጥበት  መንገድ ሊመቻች እንደሚገባም ጠቅሷል።  

በአዲስ አበባ ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የግብይት ተሳታፊዎች ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን በቀለ፤ የግብይት ሥርዓቱን ለማዘመን የአትክልት እና ፍራፍሬ የግብይት ማዕከላት በተለያዩ የከተማዋ አከባቢዎች እየተገነባ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እስካሁንም በአቃቂ፣ ኮልፌና ንፋስ ስልክ ክፍለ ከተሞች ሶስት የአትክልት እና ፍራፍሬ የግብይት ማእከላት በ60 ሚሊዮን ብር ወጪ ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ጠቅሰዋል።   

በአራዳ እና ቦሌ ክፍለ ከተሞች ተመሳሳይ ማዕከላትን ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩን የተናገሩት አቶ ሰለሞን፤  ለግንባታ የተፈቀዱ ቦታዎች ከይገባኛል ጥያቄ  የፀዱ ባለመሆናቸው ግንባታውን ለማስጀመር አልተቻለም ብለዋል።

የግብይት ማእከላቱ በርካታ የሕብረተሰብ ክፍል በሚገኝባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች  አከባቢም እየተገነቡ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤  የማእከላቱ መገንባት ህብረተሰቡ የሚፈልገውን ምርት  እንዲያገኝ እና በዘርፉ የሚስተዋለውን ህገ ወጥነት ለማስቀረት ያስችላል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም