በጌዴኦና በምዕራብ ጉጂ ዞኖች አዋሳኝ አካባቢ ለተፈናቀሉ ወገኖች ሰብአዊ ድጋፍ እየተደረገ ነው

47
ዲላ ግንቦት 30/2010 በጌዴኦና በምዕራብ ጉጂ ዞኖች አዋሳኝ አካባቢ ዳግም በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ለተፈናቀሉ ወገኖች ሰብአዊ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን የጌዴኦ ዞን አስተዳደር ገለጸ፡፡ ኢዜአ ያነጋገራቸው ተፈናቃዮች በበኩላቸው መንግስት ዘላቂ መፍትሔ እንዲያበጅላቸው ጠይቀዋል፡፡ የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኃይለማርያም ተስፋዬ እንዳሉት ባለፈው ወር ተከስቶ በነበረው የፀጥታ ችግር በርካታ ዜጎች ከአካባቢው ተፈናቅለው ነበር። ችግሩን ተከትሎ በተከናወነ ሥራ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው መመለስ ቢጀምሩም በአካባቢው ፍጹም የተረጋጋ ሁኔታ ባለመኖሩ ሳይመለሱ የቀሩ ዜጎችም ነበሩ ፡፡ ሰሞኑን ዳግም በተቀሰቀሰው የፀጥታ ችግር ምክንያት በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱንና በዚህም የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልፀዋል ፡፡ ከፌዴራልና ከሁለቱ የክልል መንግስታት ጋር በመነጋገር የሀገር መከላከያ ሠራዊት ወደ አካባቢው እንዲገባ ተደርጎ የማረጋጋት ሥራ በመከናወን ላይ መሆኑንም አስታውቀዋል ፡፡ በችግሩ ምክንያት ለተፈናቀሉት በርካታ ዜጎች የምግብ፣ የመጠለያና ሌሎች ሰብዐዊ ድጋፍ በመደረግ ላይ መሆኑን ገልጸው በአሁኑ ወቅትም ከፌዴራል መንግስት የተገኘ አራት ሺህ 500 ኩንታል በቆሎ፣ ሩዝና ዱቄት እየተከፋፈለ መሆኑን አስረድተዋል። ችግሩን በጋራ ለመፍታት ከሁለቱ ክልሎችና ከፌዴራል መንግስት የተዋቀረ ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ በአሁኑ ወቅት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልፀው "ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት በጥናት ላይ የተመሰረቱ ሥራዎች ይሰራሉ" ብለዋል ፡፡ ተፈናቅለው በገደብ ወረዳ ከሚገኙ ዜጎች መካከል ወጣት ተመስገን በቀለ እንደተናገረው ቀደም ብሎ በነበረው ችግር ከነቤተሰቡ መፈናቀሉን አስታውሷል፡፡ ቤት ንብረታቸው በመቃጠሉ የ11ኛ ክፍል ትምህርቱን አቋርጦ ከቤተሰቡ ጋር እንደተፈናቀለ የገለጸው ወጣቱ አካባቢው ሲረጋጋ ቢመለስም ግጭቱ እንደገና በማገርሸቱ በድጋሚ ስለተፈናቀለ አሁን የመጠለያና የምግብ ድጋፍ እያገኘ መሆኑን ተናግሯል። "መንግስት የሀገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦችን አንድነት ለማጠናከርና ሰላም ለማስፈን እየሰራ ባለበት በአሁኑ ወቅት እኛም መብቶቻችን ተጠብቆ ከአካባቢው ሕዝቦች ጋር በሰላም እንድንኖር በመንግስት በኩል ዘላቂ መፍትሄ ሊበጅልን ይገባል" ብሏል ፡፡ ከ15 የቤተሰብ አባላት ጋር እንደተፈናቀሉ የገለጹት አቶ በቀለ ኦብሴ በበኩላቸው ከልጅነት እስከ ዕውቀት የኖሩበትን ቀዬ በፀጥታ ችግር ምክንያት መልቀቃቸውን ገልጸዋል፡፡ "ቀደም ሲል በተነሳው የጸጥታ ችግር ተፈናቅለን ነበር፤ ሰላም ወርዷል ብለን ወደ አካባቢው ብንመለሰም ዳግም ችግሩ ተከስቶ ለመፈናቀል ተዳረግን " ብለዋል ፡፡ ልማትን እንጂ ጸብን እንደማይፈልጉ የገለጹት አቶ በቀለ መንግስት ችግሩን በዘላቂነት በመፍታት በአንድነትና በሰላም የሚኖሩበትን መንገድ ፈጥኖ እንዲያመቻች ጠይቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም