በመድኃኒትና በህክምና መሳሪያዎች አለመሟላት ተቋማቱ ተገቢውን የህክምና አገልግሎት እንደማይሰጡ ባለሙያዎቹ ተናገሩ

63

ጋምቤላ ግንቦት 22 /2011 የጤና ተቋማቱ በህክምናና መድኃኒት አቅርቦት  ችግር  ምክንያት ለኅብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት እንደማይሰጡ የጋምቤላ ክልል የጤና ባለሙያዎች ገለጹ።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በበኩሉ   ችግሮቹን ለማቃለል በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

ባለሙያዎቹ በጋምቤላ ከተማ በጤና አገልገሎት አሰጣጥና በጥቅማ ጥቅም ችግሮች ላይ ባደረጉት ውይይት ላይ እንደተናገሩት በጤና ተቋማቱ የሕክምና መሳሪያዎችና  በመድኃኒት አቅርቦት ችግሮች ተገቢውን አገልገሎት እየሰጡ አይደለም።

ከተሳታፊዎቹ መካከል  ዶክተር አብደራዛቅ ሰይድ በሆስፒታል ደረጃ መሟላት የሚገባቸው የሕክምና መሣሪያዎች ባለመኖራቸው ሕዝቡ የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት ለመስጠት መቸገራቸውን ገልጸዋል።

የፉኝዶ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል መሰጠት ከሚገባቸው 13 የሕክምና አገልግሎት መካከል ስድስቱን ብቻ እየሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።  

''በቂ ባለሙያዎች ላይኖር ይችላሉ። ይሁን እንጂ ባሉትም ቢሆንበሕክምና መሣሪያዎችና መድኃኒት አቅርቦት ችግር ለኅብረተሰቡ ተገቢው የህክምና አገልግሎተ እየተሰጠ አይደለም'' ያሉት ደግሞ ሌላው ተሳታፊ አቶ ሐብታሙ ቢያድግልኝ ናቸው።

የሕክምና መሣሪያዎች ቢመጡም ሳይተከሉ ለብልሽት እየተዳረጉ እንደሚገኙና ለአብነትም በጋምቤላ ሆስፒታል ብቻ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የሕክምና መሣሪያዎች ሳየተከሉ ከአራት ዓመታት በላይ ማስቆጠራቸውን ገልጸዋል።

 ሌላው ተሳታፊ ዶክተር ሔሬጎ አበራ በሰጡት አስተያየት በጥቃቅን የሕክምን መሣሪያዎች  ችግር ታካሚዎችን ሕይወታቸውን እያጡ መሆናቸውን ይናገራሉ።

ከዚህም በተጨማሪ የትርፍ ስዓትና የሙያ አበል ክፍያ በተደጋጋሚ ሰጠየቅም፣''በጀት የለም'' እየተባለ ክፍያው እንደማይፈጸምላቸው  አመልክተዋል።

ሌላው ተሳታፊ አቶ ሮን ጎኝ በሰጡት አስተያየት ደመውዝም ሆነ የትርፍ ስዓት ክፍያ መዘግየት ባለሙያዎች በአገልገሎት አሰጣጥ ላይ  ተጽዕኖ እየፈጠረ ነው ብለዋል።

በመሆኑን መንግሥት በጤና ባለሙያዎች ያለውን ችግር በመገንዘብ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ  ጠይቀዋል።

የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ አቶ ካን ጋልዋክ በጤና ባለሙያዎች የተነሱትን የጥቅማ ጥቅም ጥያቄዎች በአገር አቀፍ ደረጃ በሚተገበረው በታቀደው መመሪያ መሠረት ይፈታል ብለዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት በተለይም የጋምቤላ ሆስፒታልን ጨምሮ በአራት ሆስፒታሎች ያሉት  የሕክምና መሣሪያዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲተከሉ ይደረጋል ብለዋል።

በጤና ተቋማቱ ያሉት የሕክምና መሣሪያዎችም ሆነ የመድኃኒት አቅርቦት ችግሮች  ለመፍታት የክልሉ መንግሥት በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ከክልል እስክ ወረዳ የሚገኙ የአመራር አካላት የባለሙያዎችን ጥቅማ ጥቅም ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጡ አስገዳጅ ሁኔታዎች ያስቀመጣል ብለዋል።

 በውይይቱ  ከ200 በላይ የጤና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም