ሶስተኛው ምዕራፍ የኢትዮጵያ ማኅበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም በይፋ ተጀመረ

96

ግንቦት 22/2011 ፕሮግራሙ የአውሮፓ ኅብረት፣ የስዊድን ኤምባሲና የኦስትሪያ የልማት ኤጀንሲን ጨምሮ የልማት አጋሮች ባደረጉት የ30 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ የሚተገበር ነው።
ፕሮግራሙ የማኅበራዊ ተጠያቂነት መሳሪያዎችና ዘዴዎች በዜጎች፣ በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና በመንግስት አካላት ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ መሰረታዊ አገልግሎቶች ፍትሃዊ፣ ውጤታማ፣ ምላሽ ሰጪና ተጠያቂነት የሰፈነባቸው እንዲሆኑ የማስቻል ዓላማ አለው።

የኢትዮጵያ ማህበራዊ ተጠያቂነት አገር አቀፍ ፕሮግራም የትምህርት፣ የጤና፣ የመጠጥ ውሃ፣ የገጠር መንገድና የግብርና አገልግሎት ዘርፎችን ተደራሽነትና ጥራት የተመለከተ ውይይት ይካሄድበታል።

ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የሚተገበር ሲሆን የገንዘብ ድጋፉ ፕሮግራሙን በወረዳ ደረጃ ለሚተገብሩ ከ100 በላይ አገር በቀል የበጎአድራጎት ድርጅቶች እንደሚከፋፈል ተገልጿል።

 የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አድማሱ ነበበ ፕሮግራሙ መሰረታዊ ማህበራዊ አገልግሎቶች እንዲስፋፉ ከማስቻሉ በተጨማሪ የሰው ልማትን ማዕከል ያደረገ ድህነት ተኮር መርሃ ግብር የያዘ ነው ብለዋል።

ጥራት ያለው አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆንና ኀብረተሰቡ መብትና ግዴታውን እንዲለይ የሚያስችል እንደሆነም አብራርተዋል።

በሙከራ ደረጃና በሁለተኛው ምዕራፍ ትግበራ ወቅት ጠያቂ ኀብረተሰብ እንዲፈጠርና አገልግሎት ሰጪው ጥራት ያለው ግልጋሎት እንዲሰጥ የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።

የትምህርት ሽፋንና የጤና ተደራሽነት መጨመሩ፣ የመንገድ ተደራሽነት የአፍሪካ አገራት ያሉበት ስታንዳርድ ላይ ተቀራራቢ እየሆነ መምጣቱን በፕሮግራሙ ከመጡ ለውጦች መካከል ጠቅሰዋል።

የፕሮግራሙ የቡድን መሪ ሮልፍ ሆኒክ በበኩላቸው መርሃ ግብሩ ቀደም ሲል በአገሪቱ በሚገኙ 223 ወረዳዎች በአምስት ዘርፎች የተተገበረ መሆኑን ገልጸዋል።

በምዕራፍ ሶስት ትግበራ የወረዳዎቹ ቁጥር 500 እንደሚደርስና እስካሁን በወረዳ ሲተገበር የነበረው የማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም በዚህኛው ምዕራፍ በፌዴራልና ክልል ደረጃ እንደሚተገበር ተናግረዋል።

ፕሮግራሙን ለመተግበር ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በሌሎች አምስት አካባቢዎች ቢሮ ለመክፈት እየተሰራ ነውም ብለዋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም