የጎርፍ መከላከያ ሥራ ባለመሰራቱ ስጋት ውስጥ ወድቀናል….የደቡብ ወሎ ዞን ነዋሪዎች

246

ግንቦት 22/2011 በደቡብ ወሎ ዞን በክረምት ወቅት በተደጋጋሚ የሚከሰተውን ጎርፍ መከላከል የሚያስችል የክትርና የግድብ ሥራ አለመከናወኑ ስጋት ውስጥ እንደከተታቸው አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

በተደጋጋሚ በህብረተሰቡ ላይ ጉዳት በሚያደርሱ ወንዞች ላይ በ13 ሚሊዮን ብር የቅድመ መከላከል ሥራ ለመስራት ዝግጅት መደረጉም ተመልክቷል፡፡

ለኢዜአ አስተያየታቸውን ከሰጡ ነዋሪዎች መካከል በሐይቅ ከተማ ቀበሌ 04 የሚኖሩት  አቶ መሀመድ መኪ እንደገለጹት በየዓመቱ በክረምት ወቅት በሚጥለው ከባድ ዝናብ  በጎርፍ በተደጋጋሚ ጉዳት ሲደርስባቸው መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

በአካባቢው ካለ ተራራ የሚመጣውን ጎርፍ ሁሉ ጠቅልሎ ወደ ቀጤ ወንዝ የሚወስደው  ከአራት ኪሎ ሜትር በላይ ካናል በደለል ተሞልቶ ጎርፉ ወደ ቤታቸው በመግባት ጉዳት  ሲያደርስባቸው መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

ለሚመለከተው አካል ችግሩን ቢያሳውቁም መፍትሄ በማጣታቸው በሚያዚያና ግንቦት  ወር 2011 ዓ.ም ብቻ ሦስት ጊዜ በጎርፍ መጠቃታቸውን ተናግረዋል፡፡

ወደ መኖሪያ ቤታቸው በገባው ጎርፍ ከ36 ሺህ ብር በላይ የሚገመት የቤት እቃ  የወደመባቸው ሲሆን ችግሩ በመባባሱ ለሕይወታቸው መስጋታቸውንም ገልጸዋል፡፡

መንግስት ጉዳቱን በዝምታ ከመመልከት ውጭ መልሶ የማቋቋምም ሆነ ዳግም  እንዳይከሰት የመከላከል ሥራ ባለመጀመሩ ስጋታቸውን እንዳበረታው አመልክተዋል።

በአምባሰል ወረዳ የቀበሌ 03 ነዋሪ አቶ አራጋው ሰይድ በበኩላቸው ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ  በየዓመቱ በአካባቢያቸው የሚገኘው የአጀዋ ወንዝ በጎርፍ ሞልቶ አቅጣጫውን እየሳት  በእንስሳቶቻቸውና በሰብላቸው ላይ ጉዳት የሚያደርስበት ሁኔታ መኖሩን አስታውሰዋል።

ባለፈው ዓመትም በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ የተከሉትን ብርቱካን ሙሉ በሙሉ  እንዳወደመባቸው ነው የተናገሩት።

ከብርቱካን ተክሉ ከ280 ኩንታል በላይ ምርት ይጠብቁ እንደነበረ የተናገሩት አቶ  አራጋው፤ በወቅቱ የአካባቢው ማህበረሰብ ጎርፉን ለመከላከል ጥረት ቢያደርግም ወንዙ  ጠንካራ በመሆኑ መከላከል እንዳልተቻለ አስታውሰዋል፡፡

በየዓመቱ በጎርፍ ምክንያት የሚጎዳው ማሳ ከምርት ውጭ እንዳደረጋቸው የሚናገሩት  አቶ አራጋው እርሳቸውን ጨምሮ 40 አርሶ አደሮች የጉዳቱ ሰለባ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ዘንድሮም ከፍተኛ ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ገልጸው መንግስት በጥናት ላይ የታገዘ  የመከላከል ሥራ በመስራት ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

ከዚህ በፊት የሚሰራው የመከላከል ሥራ ችግሩን በተወሰነ ደረጃ ያቃልለው እንደነበር ተናግረው፤ “ዘንድሮ  እስካሁን ድረስ ምንም አይነት የመከላከል ሥራ አለመጀመሩ  ለከፍተኛ ስጋት ዳርጎናል” ብለዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽህፈት ቤት የቅድመ  ማስጠንቀቂያና ምላሽ ባለሙያ አቶ ጉግሳ ከበደ በበኩላቸው የክረምቱ ጎርፍ በህብረተሰቡ ላይ ጉዳት ሲያደርስ እንደነበር ቢታወቅም የመከላከል ስራው  በበጀት እጥረት ምክንያት መዘግየቱን ተናግረዋል፡፡

ዞኑ ከክልሉ ጋር ተቀናጅቶ የመከላከል ሥራ እስከሚሰራ ድረስ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ የየወረዳው አስተዳደር በራሱ በጀት የመከላከል ሥራ እንዲሰራ አቅጣጫ ተቀምጦ ወደ  ሥራ መገባቱን አስረድተዋል።

በተለይ በአምባሰል፣  ኮምፖልቻ፣ ቃሉ፣ ሐይቅና ተሁለደሬ ወረዳዎች በደራሽ ወንዝ  ሙላት አቅጣጫቸውን በሚስት ጎርፍ ንብረት፣ መሰረት ልማትና ሰብል በተደጋጋሚ ጊዜ እየወደመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

“በእነዚሁ ወረዳዎች በጥናት በተለዩ አጀዋ፣ ሚሌ፣ አልጌ፣ ጦጢት፣ ጃሬና ቦርከና  በተባሉ ስድስት ወንዞች ላይ በ13 ሚሊዮን ብር የመከላከል ሥራ ለመጀመር የዝግጅት  ስራ ተጠናቋል” ብለዋል፡፡

በእዚህም አቅጣጫ ስተው ለሚወጡ ወንዞች መገደቢያ መስራት፣ የተዘጉ ማፋሰሻዎችን መክፈት እንዲሁም ክትርና ግድብ መስራት ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ  ጎን ለጎንም ህብረተሰቡን በማስተባበር አካባቢን ከጎርፍ እንዲከላከል እየተደረገ  መሆኑን ነው የገለጹት።

ባለፈው ዓመት በአካባቢው በደረሰ የጎርፍ አደጋ 2 ሺህ ሄክታር በሚጠጋ መሬት ላይ  የለማ ሰብል፣ ከ5 በላይ የጤና ተቋማት እንዲሁም ከ10 በላይ ትምህርት ቤቶችና ሌሎች ንብረቶች ላይ ጉዳት መድረሱን የጽፈት ቤቱ መረጃ ያሳያል።