ጠቅላይ ሚኒስት አብይ አህመድ ለጨምበላላ በዓል የ"እንኳን አደረሳችሁ" መልዕክት አስተላለፉ

76

ግንቦት 22/2011 ጠቅላይ ሚኒስት ዶክተር አብይ አህመድ የሲዳማ የዘመን መለወጫ ጨምበላላ በዓል ምክንያት በማድረግ ዛሬ የ"እንኳን አደረሳችሁ" መልዕክት አስተላለፉ። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ዛሬ ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት፤ በሲዳማ የዘመን አቆጣጣር ጥበብ ውስጥ እስከ ማይክሮ ሰከንድ ሽርፍራፊ የጊዜ ቅንጣት ድረስ የሚወርድ ጊዜን የመለኪያ ጥበብ አለ።

ይህ ደግሞ ለ"ሲዳማ አባቶች ያለንን ክብርና ፍቅር እጅጉን ከፍ ያደርገዋል" ብለዋል።

ይሄንን የሲዳማ ሕዝብ የአዲስ ዓመት በዓልና የዘመኑን አዲስነት ለማወጅ ጊዜን የሚቆጠርበት ግሩም ዕሴት መላው የኢትዮጰያ ወገኖችን ክብሩንም ሆነ በዓሉን ከልብ ይወደዋል ወዶም እንደ ሁል ጊዜ በጋራ ያከብረዋል።

ዶክተር አብይ በመልዕክታቸው፤ ከራስ የሚነሳ የዘመን ቀመር ባለቤት  ለመሆን መቻል ያለጥርጥር  ታላቅነት ነው። ይህም ሆኖ ባሰሉት ዘመን  መስመር ላይ ዘመን የሚሻግርና "የእኛን የልጆቻችንን የዘመን ካባ የሚያተያይ ደማቅ አሻራ ለማኖር መቻል ደግሞ ከታላቅነት የሚልቅ ታላቅነት ነው" ብለዋል።

ከዋዜማው የፍቼ ትዕይንት እስከ ዋናው የጨምበላላ በዓል ድረስ አስደማሚ የዘመን መለወጫ የአከባበር ሂደት መኖሩን ጠቁመው፤ በዓሉ ሁሌም እንደ  አዲስ  የሚያስደምም  ግሩም ስርዓት እንዳለው ተናግረዋል።

የሲዳማ ሕዝብ በዘመናት ቅብብሎሽ በሚደንቅ ጥበብ ጠብቆ ያቆየው መሆኑን ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለዚህ 'ዘመን አይሽሬ የአገርና የዓለም ህያው  አእምሯዊ ሀብት ያለንን ከፍ ያለ ክብር እና አድናቆት ለመግለጽ እወዳለሁ' ብለዋል።

ዘመኑ የሰላም ፣የፍቅርና የአንድነት እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን መግለጻቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም