ክረምቱን ቀድመው ወደ ቀዬአቸው መመለስ እንደሚፈልጉ የምዕራብ ጎንደር ተፈናቃዮች ገለጹ

57

ግንቦት 21/2011 በምዕራብ ጎንደር ዞን ተከስቶ በነበረው ግጭት የወደሙ ቤቶችን መልሶ በመገንባት የማቋቋም ስራው በመጓተቱ መስጋታቸውን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የዞኑ ተፈናቃዮች ተናገሩ።

የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ለማጠናከር የተከናወኑ ስራዎች ጊዜ ቢወስዱም እስከ ሰኔ አጋማሽ ሁሉም ተፈናቃይ ወደ ቀዬው ይመለሳል ሲል የዞኑ አስተዳደር አስታውቋል። 

የገንዳውኃ ከተማ ተፈናቃይ የሆኑት አቶ ብርሃኑ መኮንን እንደተናገሩት በአካባቢያቸው በተፈጠረው አለመረጋጋት ከጥቅምት 25/2011 ዓ.ም ጀምሮ ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያ እንዳሉ ተናግረዋል፡፡

ከግጭቱ በኋላ የመልሶ ግንባታውና ወደ ቀደመ ቀያቸው የመመለሱ ስራ ዘገምተኛ በመሆኑ ከአምሰት የቤተሰብ አባላቸው ጋር አሁንም ከተማው በሚገኘው መከላከያ ካምፕ ተጠልለው እንደሚገኙ ገልጸዋል።

“መንግስት ፈጣን እርምጃ በመውሰድ እስከ አሁን ሙሉ በሙሉ ወደ ቀደመው ቀያችን መመለስ ነበረብን” ያሉት አቶ ብርሃኑ አሁንም ክረምቱ ከመግባቱ በፊት የግንባታ ስራውን ተጠናቆ ለመመለስ እንደሚፈልጉ አስረድተዋል።

በመተማ ዮሃንስ ከተማ ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ የሚገኙት አቶ ድግስ ፈንቴ በበኩላቸው “በግጭቱ የወደሙ ቤቶችን መልሶ መገንባትና የተፈናቀሉትን በወቅቱ መመለስ ባለመቻሉ በቀጣይ የእርሻ ስራቸን ላይ ጫና አሳድሯል”ብለዋል።

“ከዚህ በፊት ማሳ የማፅዳት ስራ መስራት ነበረብኝ ነገር ግን ይህን ማድረግ አልቻልኩም” ያሉት አቶ ድግስ ቀጣይ የእርሻ ጊዜ ሳያልፍ የመልሶ ግንባታው እንዲሰራና በልማት ስራቸው ተሳታፊ እንዲሆኑ ጠይቀዋል።

በቋራ ወረዳ በርሜል ቀበሌ ተፈናቃይ የሆኑትና በአርባባ የመጠለያ ጣቢያ የሚገኙት አቶ አስማረ አዱኛ በበኩላቸው “ማዕከላዊ ጎንደር ዞን አብዛኛውን መመለስ ሲቻል በምዕራብ ጎንደር ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ አይደለም”ብለዋል።

“የቋራን ህዝብ አውቀዋለሁ የሚያስተባብረው የመንግስት አካል ካለ አብሮት የነበረውን ቤት ለመገንባት ወደ ኋላ አይልም” ያሉ ሲሆን በዞኑ አስተዳደርና በክልሉ መንግስት በኩል ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ጠቁመዋል።

“ዞኑ ለሀገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ሊያስገኙ የሚችሉ ሰሊጥ፣ ጥጥና ቦሎቄ አይነት ሰብሎች የሚመረቱበት በመሆኑ መልሶ የማቋቋም ስራው ቅድሚያ ተሰጥቶት ሊፈታ ይገባል”ብለዋል።

የዞኑ የህዝብ ሰላምና ደህንነት ጉዳዮች መመሪያ ሃላፊና ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ደሳለኝ ጣሰው በበኩላቸው ግጭቱን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት ሲባል መልሶ ከማቋቋምና የተፈናቀሉትን ከመመለስ ቀድሞ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን የማጠናከርና እርቀ ሰላም የማውረድ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል፡፡

“አካባቢው ሰላም እንዳይሆን በሚፈልጉ ሃይሎች ሴራ ለዘመናት አብረው በነበሩ የቅማንትና የአማራ ህዝቦች መካከል ጥርጣሬ እንዲኖር ተደርጎ ነበር” ያሉት ምክትል አስተዳዳሪው በተሰራው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ስራ ተፈጥሮ የነበረ ችግር ተቀርፏል።

በዞኑ በግጭቱ ጉዳት ከደረሰባቸው ሁለት ሺህ 800 ቤቶች ማካከል ባለፉት ሶስት ሳምንታት ብቻ 340 ቤቶችን መልሶ በመገንባት የማስፈር ስራ እየተከናወነ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡በግጭቱ ከአካባቢው ቤቶቻቸው ፈርሰው ከተፈናቀሉ 30 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች መካከል እስካሁን ስምንት ሺህ የሚሆኑት መመለሳቸውን ተናግረው ከነዚህ ውስጥም 800 የመንግስት ሰራተኞች እንደሚገኙበት አስረድተዋል።

“ሁሉንም በዞኑ የተፈናቀሉ ወገኖች እስከ ሰኔ አጋማሽ ወደ ነበሩበት ቀየ እንዲመለሱ በማድረግ ከዚህ በፊት ይሰሩ በነበሩበት የስራ መስክ እንዲሰማሩና ልማታቸውን እንዲያከናውኑ ይደረጋልም” ብለዋል፡፡

በዞኑ በአብዛኛው የእርሻ ስራ የሚጀመረው ከሰኔ 20 በኋላ በመሆኑም በግብርናው ላይ ያን ያክል ከፍተኛ ጫና እንደማያሳድር ነው ምክትል አስተዳዳሪው የተናገሩት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም