ኢትዮጵያ በመንግስታቱ ድርጅት ሃቢታት ፕሮግራም በስራ አስፈፃሚ ቦርድ አባልነት ተመረጠች

84

ግንቦት 20/2011 ኢትዮጵያ አፍሪካን በመወከል በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሃቢታት ፕሮግራም በስራ አስፈፃሚ ቦርድ አባልነት ተመረጠች። 

በኬኒያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለኢዜአ እንዳስታወቀው፤ ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር እስከ 2022 ድረስ ለአራት ዓመታት በስራ አስፈፃሚ ቦርድ አባልነት ታገለግላለች።

ናይሮቢ እየተካሄደ ባለው ጉባኤ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ የሚመሩት የልዑካን ቡድን እና በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር መለስ ዓለም በመሳተፍ ላይ ናቸው።

ኢትዮጵያ የአፍሪካን አቋም በመደገፍና በማራመድ በኩል ባላት የፀና አቋም አፍሪካዊያን ለቦታው እንዳጯት ታውቋል። 

ጉባዔው ያደረገው ምርጫ ኢትዮጵያ በአፍሪካዊያን ዘንድ ያላት የላቀ ተቀባይነት መቀጠሉን ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል።

ኢትዮጵያም ምስጋናዋን በስራ አስፈፃሚ ቦርዱ ላይ የአፍሪካን አቋም በማንፀባረቅ እንደምትገልጽ ነው ከኤምባሲው ያገኘነው መረጃ የሚያመለክተው።

የኬኒያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ በጉባኤው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተቋማት ከተሞችን በዘላቂነት ለማልማትና ለማሳደግ የሰዎችን አሰፋፈርም ሆነ ከተሞችን ለመለወጥ በሚያስችል መልኩ ስትራቴጂዎችን መቅረጽ ይጠበቅባቸዋል።

ናይሮቢ መቀመጫውን ያደረገው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሃቢታት ፕሮግራም በማደግ ላይ ባሉ አገሮች እየታየ ካለው ፈጣን የከተሞች ዕድገት ጎን ለጎን የአቅርቦትና አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ማሳደግ ስለሚቻልባቸው መንገዶች ስትራቴጂካዊ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል።

“በከተሞች እና ማህበረሰቦች ውስጥ ለተሻሉ የኑሮ ደረጃዎች ፈጠራ” አስፈላጊነት ላይ ትኩረት ያደረገው ስብሰባ እስከ ግንቦት 23 ቀን 2011 ዓም ድረስ የሚዘልቅ ነው።

ጉባኤው ትናንት በኬኒያ ሲከፈት ከ116 አገሮች የመጡ 40 ሚኒስትሮችና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት የተገኙ ሲሆን፤ ሶስት ሺህ የሚሆኑ እንግዶች ታድመውበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም