ታላቁ የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን ከጦር ግንባር ውጊያ በላቀ ገድል እየሰሩበት ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ

91
አዲስ አበባ ሚያዝያ 23/2010 ታላቁ የህዳሴ ግድብ የአገሪቱ ህዝቦች ከጦር ግንባር ውጊያ በላቀ ገድል እያሰሩብት ያለ ፕሮጀክት እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ። ዛሬ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ በሚካሄድበት በጉባ ተገኝተው ስራውን ጎብኝተው ሰራተኞቹን አበረታተዋል። ከዚያ መልስ ከአሶሳ ከተማና አካቢዋ ነዋሪዎች ጋር ውይይት እያደረጉ ነው። በውይይታቸው መጀመሪያ ስለ ህዳሴ ግድብ ጉብኝታቸው ሲናገሩ ስራው ከጦር ሜዳ ውጊያ በላይ ትግል የሚጠይቅ እንደሆነ ጠቁመዋል። በስፍራው ሌት ተቀን እየሰሩ ታሪካዊ አሻራቸውን እያሳረፉ የሚገኙትን ሰራተኞች ''ጀግኖች ናቸው'' ብለዋል፤ ህዝቡም እንዲያመሰግንላቸው ጠይቀዋል። ግድቡ ሲያልቅ ከሚሰጠው ኢኮኖሚያ ጠቃሜታ ባለፈ የአገሪቱን ህዝቦች አንድነትና መቀራረብ እውን እያደረገ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቤኒሻንጉል ክልል ህዝብ ከሌላው የአገሪቱ ህዝብ ጋር በስፋት እንዲተዋወቅ በር የሚከፍት ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስተሩ በአሁኑ ወቅት በአሶሳ ከተማ ከነዋሪዎቹ ጋር ውይይት በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ከበዓለ ሲመታቸው ማግስት ጀምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በመዘዋወር የህዝቡን ጥያቄ በማዳመጥ በጋራ መፍትሄ ማምጣት በሚቻልበት ሁኔታ እየመከሩ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም