ጽህፈት ቤቱ የመጀመሪያውን ፕሮጀክት ፕሮፖዛል ይፋ ሊያደርግ ነው

141

ግንቦት 20/2011 የኢትዮጵያ ትረሰት ፈንድ ጽህፈት ቤት የመጀመሪያውን ፕሮጀክት ፕሮፖዛል ይፋ ሊያደርግ መሆኑን ገለጸ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በውጭ አገር ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ሁለተናዊ ልማትና እድገት ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ ማቅረባቸው የሚታወስ ነው።

ይህንንም ተከትሎ የዳያስፖራው ማህበረሰብ አባላት በቀን ከአንድ የአሜሪካን ዶላር ጀምሮ በማዋጣት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ፕሮጀክቶችን የሚደግፉበት አሰራር መዘርጋቱም የሚታወስ ነው።

በተጨማሪም በከፋ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችን የሚረዱበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ይቻል ዘንድ ''ኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረሰት ፈንድ'' የተሰኘ ጽህፈት ቤት ተመስርቶ በርካታ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት አቅማቸው የፈቀደውን ያህል መዋጮ በትረስት ፈንዱ ስም በተከፈተው የባንክ አካውንት ገቢ በማድረግ ለወገንና ለአገራቸው ያላቸውን ደራሽነት እያስመሰከሩ ይገኛሉ።

በዚህም መሰረት ጽህፈት ቤቱ የተሳትፎ ጥሪውን የበለጠ ለማሰማት የሚያስችለውና የመጀመርያውን የፕሮጀክት ፕሮፖዛሎች ይፋ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡

ከዚህም ጋር ተያይዞ ከተለያዩ ባላድርሻ አካላት ጋር በመወያየት ግንዘቤን ለማስጨበጥ፣ የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ ብሎም ጠቃሚ ግብአቶችን ለማሰባሰብ የሚያስችል የዳሰሳ አውደ ጥናት አዘጋጅቷል።

አውደ ጥናቱን የትረስት ፈንዱ ጽህፈት ቤት ከተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም/UNDP/ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ሲሆን ትረስት ፈንዱን በሚመለከት ለባለ ድርሻ አካላት በቂ ግንዛቤ ማስጨበጥን ያለመ ነውም ተብላል።

በተጨማሪም ድጋፍ የሚደረግባቸው ፕሮጀክቶችን በመለየት የትኩረት አቅጣጫውን ከአካባቢያዊ ክልላዊና አገራዊ ጉዳዮች ጋር በማናበብ የጋራ መግባባት ላይ መድረስና በትረስት ፈንዱ ፕሮፖዛል ላይ ጥልቅ ውይይት በማካሄድ ግብአት ማሰባሰብ እንደሆም ተገልጿል።

አውደ ጥናቱ ግንቦት 21 እና 22 ቀን 2011. በአዲስ አበባ ኢሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል የስብሰባ አዳራሽ  እንደሚካሄድም ተጠቁሟል። 

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ በአሜሪካን ሀገር ተመዝግቦ ህጋዊ ሰውነት ያገኘ ሲሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ለመንቀሳቀስ የሚያስችለውን ህጋዊ የምዝገባ ሂደት በማከናወን ላይ የሚገኝ ግብረ ሰናይ ተቋም ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም