ሶስተኛው ዙር ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር ተጀመረ

56
አዲስ አበባ ግንቦት 30/2010 ሶስተኛው ዙር ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር ዛሬ በጎንደር ከተማ ተጀመረ ። እስከ ሰኔ 3 ቀን 2010 ዓ.ም በሚደረገው ውድድር በሁለቱም ጾታዎች ከስምንት ክለቦች የተወጣጡ 80 ተወዳዳሪዎች ይሳተፋሉ። አዲስ አበባ ፖሊስ፣ ፌዴራል ፖሊስ፣ ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች፣ የኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ ክለቦች እንዲሁም ማራቶን፣ ድሬዳዋ ከነማ፣ ጎንደር ከነማና የኢትዮ-ሶማሌ የቦክስ ቡድኖች በውድድሩ የሚሳተፉ ናቸው። ውድድሩ የኢትዮጵያ የቦክስ ፌዴሬሽን ዘንድሮ ከሚያካሂዳቸው ብሔራዊ የክለቦች የቦክስ ውድድሮች ሶስተኛው ነው። የፌዴሬሽኑ የውድድርና ስልጠና ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ስንታየሁ ተስፋዬ ለኢዜአ እንደገለጹት ተተኪ ቦክሰኞችን ለብሔራዊ ቡድን በመምረጥ ስልጠና እንዲያገኙ በማድረግ በስፖርቱ የተሻሉ ተወዳዳሪዎችን ማፍራት የውድድሩ ዓላማ ነው። የቦክስ ክለቦችን የውድድር አማራጭ ማስፋትና አቋማቸውን እንዲፈትሹ ለማድረግ ውድድሩ እንደሚያግዝ አቶ ስንታየሁ ገልጸው ስፖርቱንም ለማስፋፋት የበኩሉን አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል። በወንዶች ከ49 እስከ 91 ኪሎ ግራም፤ በሴቶች ደግሞ ከ48 እስከ 60 ኪሎ ግራም ክብደቶች ውድድሮች ይካሄዳሉ። የመጀመሪያና የሁለተኛ ዙር ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድሮች በአዲስ አበባና በሆሳዕና ከተማ መካሄዱን አስታውሰው የመጨረሻው የክለቦቹ ውድድር ሰኔ መጨረሻ 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ጠቁመዋል። በቀጣይ የተሳታፊ ክለቦችን ቁጥር በመጨመር ውድድሩን የማስፋት እቅድ እንዳለም አክለዋል። በውድድሩ የመክፈቻ ቀን በ91 ኪሎ ግራም የፌድራል ፖሊሱ ሙሉቀን መልኬ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ የቦክስ ክለብ ተጫዋች የሆነው ታምራት አበበ ለፍጻሜ ይገጥማሉ። በተጨማሪም 15 የማጣሪያ ጨዋታዎች እንደሚከናወኑ የወጣው መርሃ-ግብር ያመለክታል፡፡ በኢትዮጵያ ከ1950ዎቹ ጀምሮ የቦክስ ስፖርት እንደ አንድ የስልጠና ዓይነት በጦር ኃይል ውስጥ ለወታደሮች ይሰጥ ነበር። በተለይ በሐረር ጦር አካዳሚ የሚያሰለጥኑት እንግሊዞች በመሆናቸው የቦክስ ስፖርትን እንደ ዋነኛ የስልጠና ዓይነት ይሰጡ ነበር። የክለቦች ምስረታም በዛው ወቅት የተጀመረ ሲሆን በሰራዊቱ ውስጥ ከተቋቋሙ ክለቦች መካከልም የክቡር ዘበኛ፣ መኩሪያ፣ ምድር ጦር፣ ፖሊስ፣ ፈጥኖ ደራሽ የሚባሉ ክለቦች ይጠቀሳሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም