ለ2012 አገራዊ ምርጫ ማስፈጸሚያ የ3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በጀት ተጠየቀ

86

አዲስ አበባ ግንቦት 19/2011 ለ2012 አገራዊ ምርጫ ማስፈጸሚያ የ3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በጀት መጠየቁን ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።

ከተጠየቀው በጀትም 900 ሚሊዮኑ ከአጋር ድርጅቶች የሚገኝ መሆኑ ተገልጿል።

በጀቱ ባለፈው ምርጫ ከተመደበው በጀት ጋር ሲወዳደር ከፍተኛ ብልጫ አለው።

ቦርዱ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አንዳስታወቀው በቀጣዩ ዓመት ይካሄዳል ተብሎ ለሚታሰበው አገራዊ ምርጫ የ 4 ቢሊዮን ብር የበጀት ጥያቄ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል።

ይሁንና በምክር ቤቱ የበጀትና ፋይናንሰ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጋር በተደረገ ውይይት በጀቱ ተከልሶ 3 ነጥብ 7  ቢሊዮን ብር እንዲሆን መወሰኑን ነው የቦርዱ የኮሙኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ የተናገሩት።

ለአገራዊ ምርጫው የተጠየቀው በጀት ካለፈው ምረጫ ጋር ሲወዳደር ከፍተኛ ብልጫ እንዳለው የገለጹት አማካሪዋ ለዚህ ደግሞ ምክንያቶችን ጠቅሳዋል።

ከምክንያቶቹ ውስጥም የምርጫ ኮሮጆዎችን በግልጽ በሚያሳዩ ኮሮጆዎች ለመቀየርና በአንድ ምርጫ ጣቢያ አንድ  የነበረውን ኮሮጆ ሁለት ለማድረግ ታቅዷል።

እያንደንዱ የድምጽ መስጫ ወረቀት የደህንነት መለያ ቁጥርና የተወዳዳሪ ምስልን የያዘ ከመሆኑ ሌላ የመራጮች  ቁጥርም በህዝብ ቁጥር ዕድገት መሰረት የሚሰላ ይሆናል ብለወዋል።

ከዚህ ባለፈ ገለልተኛ ምርጫ አስፈጻሚዎችን ለመመልመልና ለማሰልጠን ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑ በጀቱ  ከፍ እንዲል መደረጉ ነው የተነገረው።

የምርጫ በጀቱ ሲዘጋጅ የመራጮች ቁጥር 53 ነጥብ 9 ሚሊዮን ይደርሳል ተብሎ የተገመተ ሲሆን ከዚያ ወስጥ 45 ነጥብ 3 ሚሊዮኑ ለመራጭነት ይመዘገባል ተብሎ መታሰቡንም ነው ወይዘሪት ሶሊያና የገለጹት።

በጀቱ በአንድ ምርጫ ጣቢያ በአማካይ አንድ ሺ 500 መራጭ እንደሚመዘገብና  41 ሺ 600 ምርጫ  ጣቢያዎችንም ታሳቢ ያደረገ ነው።

ይህ በጀት የ2012 አገራዊ ምርጫን ብቻ ለማድረግ  የተጠየቀ ሲሆን ቦርዱ የገለልተኛ ተቋማት የበጀት ነጻነት  መርህን መሰረት በማድረግ ለመጀመሪያ ጊዜ ለምክር ቤቱ በቀጥታ አቅርቧል።

በበጀት ጥያቄው ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎም ይጠበቃል።

በሌላ በኩል ቦርዱ ባለፉት ስድስት ወራት ቦርዱን በህዝብ ተዓማኒ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎችን ሲያከናውን  መቆየቱን አስታውቋል።

ከዚህ ወስጥም የህግ ማዕቀፎችን ማሻሻል፣ተቋማዊ ማሻሻያዎች ማድረግ፣ለፖለቲካ ፓርቲዎች የውይይት መድረክ  መፍጠር፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ድጋፍ ማድረግ፣ የሲቪክ ማህበራት ጋር መስራት የሚቻልበትን  ሁኔታ ማሻሻል፣ የምርጫ በጀት መወሰን እንዲሁም ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር ትብብር መፍጠር ይገኙበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም