ለ2012 አገራዊ ምርጫ ውጤታማነት ከመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ጋር እሰራለሁ-ምርጫ ቦርድ

69

ግንቦት 19/2011 የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በቀጣዩ ዓመት የሚካሄደውን አገራዊ ምርጫ ወጤታማ ለማድረግ ከመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ጋር ለመስራት አንደሚፈልግ አስታወቀ።

ቦርዱ ከተቋማቱ ጋር ለመስራት በሚችልባቸው ጉዳዮች ላይ ዛሬ የግማሽ ቀን ምክክር አድርጓል።

የ2012 ዓ.ም ስድስተኛው ዙር አገራዊ ምርጫ ፍትሃዊ፣ተዓማኒና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን መገናኛ ብዙሃን የጎላ ሚና እንዳላቸው በዚሁ ጊዜ ተገልጿል።

ቀደም ሲል ቦርዱም ሆነ መገናኛ ብዙሃኑ በህዝብ ዘንድ ተዓማኒነት የጎደላቸው አንደነበር ነው በውይይቱ የተነሳው።

የቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ እንዳሉት ለቀጣይ  ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሚያደርጉት ውይይትና ክርክር ምቹ ሁኔታ መፍጠር ከመገናኛ ብዙሃን ተቋማቱ ይጠበቃል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች አማራጮችን ዜጎች በሚገባቸው ቋንቋ ትንታኔና ማብራሪያ መስጠትም ሌላ ሃላፊነት ነው  ብለዋል።

መገናኛ ብዙሃን እንደ ቦርዱ ገለልተኛ በመሆኑ በአገሪቷ ቀደም ሲል ከተደረጉ ምርጫዎች በተዓማኒነቱና በተቀባይነቱ የተሻለ ምርጫ ለማካሄድ በጋራ ሊሰሩ ይገባልም ብለዋል።

መገናኛ ብዙሃን በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫና በድህረ ምርጫ ጊዜ ምን አይነት ሚና ይኖራቸዋል? እንዲሁም  የዘመናዊ ሚዲያ ዕድሎችና ተግዳሮቶች በሚል ርዕስም የውይይት መነሻ ቀርቦ ነበር።

ቦርዱ ገለልተኛና ተዓማኒ የምርጫ አስፈጻሚነቱን ለማጠናከር ለመገናኛ ብዙሃን  በማህበራዊ ሚዲያ፣በቃለ መጠይቅና በጋዜጣዊ መግለጫዎች መረጃዎችን ለመስጠት ዝግጁ መሆኑንም ነው ያስታወቀው።

የሚዲያ ሚና ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ በሚል በተካሄደው ውይይትም የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ተቋማት ባለሙያዎችና የዘርፉ ተዋንያን ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም