የጦር መሳሪያን ለማስተዳደርና ለመቆጣጠር የሚረዳ ረቂቅ አዋጅ እየተመከረበት ነው

132

አዲስ አበባ ግንቦት 19/2011 አዋጁ የጦር መሳሪያን በህግ አግባብ ለማስተዳደር የሚያስችል ቢሆንም ከጎረቤት አገሮች ጋር በድንበር አካባቢ የሚኖረውን ማህበረሰብ ታሳቢ ማድረግ እንደሚገባ ተገለጸ።

በአገሪቱ የሚታየውን የጦር መሳሪያ ልውውጥ፣ ዝውውር፣ ማምረት፣ ፍቃድ የመስጠት ፣የጦር መሳሪያ የመቆጣጠር፣ የማስተዳደር ስልጣንና ሀላፊነትንበተመለከተ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግና ፍትህ ቋሚ ኮሚቴ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ዛሬ ውይይት አካሂዷል።

በውይይቱ ላይ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ፣ የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ፣ የፌደራልና የክልል ፖሊስ ኮሚሽን ተወካዮች ተገኝተዋል።

ከክልላቸው አንፃር ያለውን ነባራዊ የጦር መሳሪያ ሁኔታ ለቋሚ ኮሚቴው ያስረዱት የየክልሎቹ የፖሊስ ኮሚሽን ተወካዮች፤ ረቂቁ ጸድቆ ወደ ስራ ከመግባቱ በፊት ቅድሚያ መዳበርና ህብረተሰቡ እስከ ታች መወያየት እንዳለበት አሳስበዋል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አሁን ባለው አቅም በአገሪቱ የሚገኘውን የጦር መሳሪያ ለማስተዳደርና ለመቆጣጠር ይከብደዋል ያሉት የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮማንደር አበረ አዳሙ፤በተለይም የፌደራል ፖሊስን ለማስገባት ፈቃደኛ በማይሆኑ ክልሎች ላይ አዋጁን ለማስፈፀም አዳጋች ነው ብለዋል።      

ከትግራይ፣ ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች፣ ጋምቤላ፣ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ እንዲሁም ከአፋር ክልል የተገኙ የክልል ፖሊስ ኮሚሽን ተወካዮች ደግሞ አዋጁ መርቀቁ የጦር መሳሪያን በህግ አግባብ ለማስተዳደር የሚያስችል ቢሆንም ከጎረቤት አገሮች ጋር በድንበር አካባቢ የሚኖረውን ማህበረሰብ ታሳቢ አላደረገም ብለዋል።

ስለሆነም አዋጁ ጸድቆ ወደ ስራ ከመግባቱ በፊት የእያንዳንዱ ክልል ማህበረሰብ ለጦር መሳሪያ የሚሰጠውን ቦታና ባህል ታሳቢ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

ጊዜ ተሰጥቶት አዋጁ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች መሰራት እንዳለባቸውም የየክልሎቹ ፖሊስ ኮሚሽን ተወካዮች የተናገሩት።  

የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው አዋጁ በአፈጻጸም ላይ ክፍተት እንዳይፈጠር መካተት ያለባቸውን ዝርዝር ነጥቦች እንዲያካትት የፌደራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግን ጠይቀዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጁ በተለያየ መንገድ ወደ አገሪቱ የገባውንና በግለሰቦችና በድርጅቶች እጅ የሚገኝን የጦር መሳሪያ በህግ አግባብ ለማስተዳደርና ለመቆጣጠር  ያስችላል ተብሏል።

አዋጁ የጦር መሳሪያ የማስተዳደርንና የመቆጣጠርን ስልጣን ለፌደራል ፖሊስ የሚሰጥ ሲሆን በህገመንግስቱ በተሰጠው የውክልና ስልጣን መሰረት በክልል ፖሊስ ኮሚሽኖችም ተፈጻሚ እንደሚሆን በውይይቱ ላይ ተገልጿል።  

አዋጁን ለማስፈፀም ደንብና መመሪያ ተጠናቆምበሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ  በአገሪቱ ያለ የጦር መሳሪያ በመለያ እንደሚመዘገብ ተጠቅሷል።

ቋሚ ኮሚቴው በረቂቁ ላይ ግብዓቶችን ለማሰባሰብ የሚረዳውን ተጨማሪ ውይይት ከባለድርሻ አካላት ጋር ለማከናወን ለግንቦት 28 ቀን 2011 ዓ.ም ቀጠሮ ይዟል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም