በኢትዮጵያ ኢልኒኖ የተሰኘው የአየር መዛባት ሊከሰት እንደሚችል ተገለፀ

68

አዲስ አበባ ግንቦት 19/2011 በኢትዮጵያ በመጪው የክረምት ወቅት ኢልኒኖ የተሰኘው የአየር መዛባት በአነስተኛ መጠን ሊከሰት እንደሚችል የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሚቲዮሮሎጂ ኤጀንሲ ገለጸ።
ይሁን እንጂ በደካማ በሆነው ኢልኒኖ የአየር መዛባት ምክንያት ሊከሰት የሚችለው ድርቅ ከህንድ ውቅያኖስ በሚነሳው እርጥበታማ አየር ይካካሳል የሚል እምነት እንዳለም ኤጀንሲው አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ከኢጋድ የአየር ትንበያና ምልከታ ማዕከል ቀደም ብሎ የዓለም አቀፍ ሞዴሎችን በመጠቀም የቀጣዩን ሶስት ወር የአየር ትንበያና ትንተና ጥናት አጠናቋል።

በዚህየትንበያትንተናመሰረትበሰሜንምስራቅ የአገሪቱ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በታች የሆነ ዝናብ እንደሚኖር የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ ለኢዜአ አስታውቀዋል።

በደቡብ አጋማሽ የአገሪቱ ክፍሎች በተወሰኑ አካባቢዎች መደበኛ የሆነ ዝናብ ሊያገኙ እንደሚችሉ መተንበዩንም ገልጸዋል።

በመሆኑም የዚህ አይነቱ የዝናብ ስርጭት ድምር በአገሪቱ ደካማ ወይም ዝቅተኛ መጠን ያለው ኤሊኒኖ የአየር መዛባት ሊከሰት እንደሚችል ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል።

በደካማ ኢልኒኖ መከሰት ምክንያት ድርቅ ሊፈጠር የሚችልበት አጋጣሚ ቢኖርም ከህንድ ውቅያኖስየሚመጣው አየር የእርጥበት መጠኑን በማጠናከር አወንታዊ ሚናው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ  መደበኛና ከመደበኛ በታች ዝናብ በሚያገኙ የሰሜን ምስራቅ የአገሪቱ አካባቢዎች የተለየ ድጋፍ ሊሰጣቸው ይገባል።

በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ከሰኔ እስከ መስከረም ባሉት ሶሰት ወራት የሚኖረው የዝናብ ስርጭት ከመደበኛው በታች ሊሆን እንደሚችልም ተገልጿል።

አጠቃላይ የቀጠናው የዝናብ ስርጭት፣ ትንበያና ትንተና እንዲሁም የአየር ጠባይ ሁኔታ በነገው እለት ይፋ ይደረጋል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም