የኦሮሚያ ክልል ከ700 ሺህ በላይ ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬአቸው መመለሱን ገለጸ

111

አዲስ አበባ ግንቦት 17/2011 የኦሮሚያ ክልል ከ700 ሺህ በላይ ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬአቸው መመለሱን የክልሉ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል።

የክልሉ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ምክትል ኮሚሽነር አቶ ገረመው ኦሊቃ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በክልሉ ባለፉት 2 ዓመታት ከሶማሌ ክልልና አዋሳኝ አካባቢዎች፣ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልልና አጎራባች ዞኖች፣ ከጌዲዮ፣ ጉጂ አካባቢ ከ1ነጥብ4 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተፈናቅለዋል።

ከተፈናቀሉት መካከል ግማሽ ያህሉ ወደየቀዬአቸው ሊመለሱ መቻላቸውን አመልክተዋል።


በኦሮሚያ ክልል  ከፍተኛ የሆነ የተፈናቀዮች ቁጥር ቢኖርም በህብረተሰቡ፣ መንግስት፣ ባለሀብቶች፣ የተለያዩ አጋር ድርጅቶች ባደረጉት ርብርብ እርዳታ በማድረስ በተፈናቃዮች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳይደርስ መከላከል መቻሉን ገልጸዋል።

የተለያየ የፖለቲካ ፍላጎት ባላቸው ግለሰቦች የፖለቲካ ሴራ ምክንያት ከምስራቅ ሀረርጌ፣ ምዕራብ ሀረርጌ፣ ባሌ፣ ቦረና፣ ጉጂ፣ ምዕራብና ምስራቅ ወለጋና አጎራባች የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ተፈናቅለዋል።

መጠለያ፣ምግብና መድኃኒት በማድረስ በሰው ህይወት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ድጋፍ እንዲያገኙ መደረጉን ምክትል ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

ባለፉት ሁለት ሳምንታት ተፈናቃዮችን ወደቀዬአቸው ለመመለስና መልሶ ለማቋቋም የተደረገው ጥረት ስኬታማ እንደሆነ የገለጹት አቶ ገረመው በምስራቅና ምዕራብ ወለጋ ብቻ 200 ሺህ ተፈናቃዮች መመለሳቸውን ተናግረዋል።

ወደቀዬአቸው ሲመለሱ ምንም የሌላቸው በመሆኑ እንዳይቸገሩ ድጋፍ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል።

በምዕራብ ጉጂና በጌዲኦ ህዝቡን እርስ በርስ የሚያጋጩ ችግሮችን በማጥናትና በማወያየት ህዝቡ ወደቀዬው እንዲመለስ መደረጉን ያመለከቱት ምክትል ኮሚሽነሩ  ከደቡብ ክልል የበላይ አመራር ጋር በመሆን ችግሩን ለመፍታት መሰራቱን ገልጸዋል።

የጌዲኦ ተፈናቃዮችን ወደቀዬአቸው ለመመለስ የተደረገው ጥረት ችግር አጋጥሞት እንደነበር ገልጸው በተለያየ ጊዜ የተፈናቀሉትን በማጥናት ወደቀዬአቸው ለመመለስ ሰፊ ጥረት መደረጉን አመልክተዋል።


''በምዕራብ ጉጂና ጌዲዮ አካባቢዎችም ወደ 90 ሺህ ዜጎች ወደ ቄያቸው ተመልሰዋል፣ በአጭር ጊዜ ሁሉም ተፈናቃይ ወደ ቀዬው ይመለሳል'' ብለዋል።

ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው ሲመለሱ በፍላጎታቸው መሰረት መሆኑን የተናገሩት አቶ ገረመው፤ “ባገኘነው አጠቃላይ የዳሰሳ መረጃ ሁሉም በአንድ ድምጽ ወደ ቀዬአችን ተመልሰን ኑሯዋችንነ እንምራ የሚል ነው'' ብለዋል።


''ተፈናቃዮች በዘላቂነት እሰኪቋቋሙ ድረስ የክልልና የፌዴራል መንግስት ድጋፍ ያደርጋል'' ያሉት አቶ ገረመው ዘላቂ ሰላም እንዲኖር ወጣቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች ውይይት እያደረጉ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በህዝቦች መካከል ግጭት በመፈጠር ህብረተሰቡ እንዲፈናቀል የሚያደርጉ እና ከዚህ ተጠቃሚ የሆኑ አካላትን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ መንግስት ጥናት እያደረገ መሆኑን አመላክተዋል።

በህዝብ መካከል ጣልቃ የሚገቡትን በመለየት እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

በቀጣይ እንዲህ አይነት ችግሮች እንዳይከሰቱ ህዝቡና የጸጥታ አካል ቀድመው የመከላከል ስራ እንደሚሰሩ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በክልሉ በግጭት የተፈናቀሉትን ጨምሮ 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ህዝብ የእለት እርዳታ የሚፈልጉ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም