ዘጠኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች 'ብሔራዊ ግንባር' ለመፍጠር የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ

106

ግንቦት 17/2011 ብሄራዊ ግንባሩን ለመፍጠር ዛሬ ስምምነት የተፈራረሙት ሁለት አገራዊና ሰባት ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲሆኑ ግንባሩን ''የኢትዮጵያ አንድነት ብሔራዊ ግንባር'' በሚል ሰይመውታል።

ተመሳሳይ አጀንዳ ያላቸው እነዚህ ፓርቲዎች ግንባር መፍጠራቸው ለህዝቡ ጠንካራ አማራጭ እንዲሆኑ የሚያስችላቸው እንደሆነ በስነ-ስርዓቱ ላይ ተገልጿል።

ግንባሩን ከፈጠሩት ፓርቲዎች መካከል የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ኮንግረስ ፓርቲ ተወካይ አቶ ገረሱ ገሳ ''የፖለቲካ ሃይሎች ከጥላቻ፣ ከዘረኝነትና ከቂመኝነት ወጥተው ሰላማዊና የተረጋጋ የፖለቲካ ምህዳር ለመፍጠር በጋራ ሊሰሩ ይገባል'' ብለዋል።

''መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በመካከላችን ያለውን የማንነትና የሀሳብ ልዩነቶችን አክብረን ተከባብረን ከውስጣችን ጥላቻን፣ ቂመኝነትን፣ በቀለኝነትን፣ ዘረኝነትን፣ ጠባብነትን፣ አግላይነትንና አፈናቃይነትን አስወግደን ለሁላችንም የጋራ ሰላምና ደህንነት እንድንቆም ጥሪ አቀርባለሁ'' ብለዋል።

የጋምቤላ ህዝቦች ነጻነት ንቅናቄ ተወካይ አቶ ታደለ ብሩ በበኩላቸው ፓርቲ የህዝብና የአገር ሃብት እንደመሆኑህዝብን ለመምራትና ለማስተዳደር የሚቋቋም መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ አንድነት ብሄራዊ ግንባርን ለመመስረት የተስማሙ ፓርቲዎች ግንባሩን ለግል ዓላማና ፍላጎት ማስኬጃ ሳይሆን ለአገርና ለህዝብ ዓላማ ማስፈፀሚያ እንዲጠቀሙበት ጠይቀዋል።

ፓርቲዎቹ ዛሬ የተፈራረሙት የስምምነቱን ዓላማ፣ ተፈጻሚነት፣ የስምምነቱ አድራጊ ፓርቲዎች ሃላፊነትና ግዴታ የጊዜያዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ሃላፊነት እንዲሁም ወደ ስምምነቱ የሚመጡ ሌሎች ፓርቲዎችን ስለመቀበልና ሌሎች ጉዳዮችን ጨምሮ ከ12 በላይ አንቀፆችን የያዘ ሰነድ ነው።

ብሄራዊ ግንባሩ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ያወጣ ሲሆን ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት አስከፊ የድህነት፣የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ችግሮች በማላቀቀቅ ዜጎቿን ከዘር ተኮር ጥቃት መከላከልን ዋና ዓላማ አድርጎ እንደሚሰራ አስታውቋል።

ግንባሩን የመሰረቱት ፓርቲዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ኮንግረስ፣ የኢትዮጵያ ህብረ ህዝብ ብሔራዊ ንቅናቄ፣ የአገው ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የጋምቤላ ህዝቦች ነጻነት ንቅናቄ፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ህብረት፣የደቡብ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኮንግረስ፣ የጋምቤላ ህዝብ ፍትህ፣ ሰላምና ልማት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣ የሸካና አካባቢው ዴሞክራሲያዊ ድርጅትና የአርጎባ ብሔረሰብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም