በወርልድ ቴኳንዶ ሻምፒዮና የሶስተኛ ቀን ውሎ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎችን አገኘ

58

ግንቦት 17/2011 በ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ሻምፒዮና የሶስተኛ ቀን ውሎ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎችን አግኝቷል።

በኦሮሚያ ክልል ለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ አስተዳደር የወጣት ማዕከል የሚካሄደው ሻምፒዮና ከትናንት በስቲያ መጀመሩ ይታወቃል።

ዛሬ በሻምፒዮናው የሶስተኛ ቀን ውሎ ሶስት የፍጻሜ ጨዋታዎች ተደርገዋል።

ከ74 ኪሎ ግራም በታች የወንዶች ፍጻሜ ጨዋታን የአዲስ አበባው ኪዳኔ መንግስቱ የደቡብ ክልሉን አድነው መለሰን በማሸነፍ የወርቅ ሜዳሊያ ሲያገኝ፤ አድነው ደግሞ የብር ሜዳሊያ ባለቤት ሆኗል።

 በዚሁ ዘርፍ የግማሽ ፍጻሚ ተሸናፊዎቹ የኦሮሚያው ማንደፍሮ ለሚና የቤኒሻንጉል ጉምዙ ከማል ኡስማን የነሐስ ሜዳሊያ ተሻላሚ ሆነዋል።

ከ63 ኪሎ ግራም በታች  ወንድ የአዲስ አበባው አብዱራማን ሰፋ የደቡብ ክልሉን አዲስ ካርሎስን በማሸነፍ የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘ ሲሆን፤ ተጋጣሚው አዲስ የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል።

በዚሁ የክብደት ዘርፍ በግማሽ ፍጻሜው የተሸነፉት የቤኒሻንጉል ጉምዙ ሙክታር በብክር እና የኦሮሚያው ይታገሱ ሃይለ ሚካኤል የነሐስ ሜዳሊያ ያገኙ ተወዳዳሪዎች ናቸው።

በዚሁ መሰረት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎችን አግኝቷል።

ከ46 ኪሎ ግራም በታች ሴቶች ውድድር የአማራ ክልሏ አክሱማዊት ፍስሃ የአዲስ አበባውን ሱመያ ዲኖን በማሸነፍ የወርቅ ሜዳሊያ ስታገኝ፤ ሱመያ የብር ሜዳሊያ አግኝታለች።

በዚሁ የክብደት ዘርፍ በግማሽ ፍጻሜው የተሸነፉት የደቡቧ ማህሌት መሰለ እና የኦሮሚያዋ ማረካን ወልደማርያም የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚዎች ሆነዋል።

ከአምስት ክልሎችና ከሁለቱ የከተማ አስተዳሮች በወንዶች 35 በሴቶች 31 በአጠቃላይ 66 ተወዳዳሪዎች በሻምፒዮናው ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በወንዶች ከ54 ኪሎ ግራም በታች ጨምሮ እስከ 80 ኪሎ ግራም በታች፣ በሴቶች ከ46 ኪሎ ግራም በታች ጨምሮ እስከ ከ67 ኪሎ ግራም በታች ያሉት ሻምፒዮናው የሚካሄድባቸው የውድድር ዘርፎች ናቸው።  

የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ሻምፒዮና ነገ ፍጻሜውን ያገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም