በክልሉ የኤች አይ ቪ ኤድስን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ጥረታችንን አናጠናክራለን -ባለድርሻዎች

98

ጋምቤላ ግንቦት 17 / 2011 በጋምቤላ ክልል የኤች አይ ቪ /ኤድስን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረገውን እንቅስቃሴ እንደሚያጠናክሩ ባለድርሻ አካላት ገለጹ። 

በሽታውን በመከላከልና በመቆጣጠር ላይ ማህብረሰብ አቀፍ ንቅናቄ  መድረክ በጋምቤላ ከተማ ተካሂዷል፡፡

በክልሉ የበሽታውን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረገው እንቅስቀሴ በማጎልበት ድርሻቸውን እንደሚወጡ የመድረኩ ተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡

በተለይም ከዚህ በፊት በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በመገናኛ ብዙኃን፣በቤተ-እምነቶች፣በወጣቶች ማህበራትና በሌሎችምአካላት የሚከናወኑ ተግባራት መቀጠል እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

ከተሳታፊዎች መካከል አቶ ኡቦንግ ኡጁቶ እንዳሉት ከዚህ ቀደም በክልሉ በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የቅስቀሳና ግንዛቤ ማሰጨበጫ ሥራዎች  መቀጠል  ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

በዚህም ኅብረተሰቡ በዘመቻ መልኩ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ምርመራ ማካሄዱን ያስታውሳሉ፡፡

ይሁንና በአሁኑ ወቅት በበሽታው ዙሪያ የሚካሄዱ የቅስቀሳና ግንዛቤ ማሳደጊያ ሥራዎችና መሥሪያ ቤቶች በሥራቸው አካተው ባለመስራታቸው ከተፈጠረው መዘናጋት መውጣት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡

ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ ወጣት ጋሻው ጳውሎስ በበኩሉ በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚካሄዱ ሥራዎች በአገር ደረጃ እየቀነሱ መምጣታቸውን ተናግሯል፡፡

በተለይም መገናኛ ብዙኃን በድራማ  በጭውውት በጽሑፍና በሌሎች መንገዶች የነበረው እንቅስቃሴ መቀዛቀዙን ጠቁሟል፡፡

በመሆኑም በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረገው ጥረት መጠናከር እንዳለበትም አመልክቷል፡፡

በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበትና በተለይም ወላጆች ልጆቻቸውን ከበሽታው ለመጠበቅ ድርሻችንን ልንወጣ ይገባል ያሉት ደግሞ ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ኡቦንግ አዋሌ ናቸው፡፡

በቀጣይ ጥረቱን ለማገዝና ኅብረተሰቡን ለማስተማር ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

ቄስ ኡጋቱ ኡጁሉ በበኩላቸው በክልሉ የሚታየውን የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል የሚደረገውን እንቅስቃሴ እንደሚደግፉ አረጋግጠዋል፡፡

በሽታውን የሚያስፋፉ በተለይም ከጋብቻ ላይ ጋብቻና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ለማስወገድ በሚደረገው እንቅስቃሴ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል፡፡

የክልሉ ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ሴክረተሪያል ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኡቦንግ ኘየል እንደተናገሩት በክልሉ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የባለድርሻ አካላት ድጋፍ መጠናከር አለበት፡፡

በተለይም የሃይማኖት ተቋማት፡የሲቪክ ማኀበራት እና ባለድርሻ   አካላት የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ ትኩረት አንዲሰጡ እሳስበዋል፡፡

በተለይም በክልሉ የቫይረሱ ስርጭት ከነበረበት 6ነጥብ 5 ወደ 4ነጥብ 8 በመቶ ማውረድ ቢቻልም፤ ትኩረት ሊነፈገው እንደማይገባ ገልጸዋል፡፡

ጽህፈት ቤቱ በቀጣይም በሽታውን ለመግታት ጥረቱን  እንደሚያጠናክር ጠቁመዋል፡፡

በጋምቤላ ክልል ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ 13ሺህ ሰዎች አሉ።

በውይይቱ ላይ በከተማዋ ከሚገኙ ከአምስቱም ቀበሌዋች የተወጣጡ የሃይማኖት አባቶች፣የአገር ሽማግሌዎች፣የጤና ባለሙያዎች፣ወጣቶችና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም