ዩኒቨርሲቲው የልማት ሥራዎች ዘላቂ እንዲሆኑ በጥናትና ምርምር ሥራዎች ድጋፍ እንዲሰጥ ተጠየቀ

274

ሶዶ ግንቦት 16/ 2011 የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ አገራዊ የልማት ሥራዎች ዘላቂ እንዲሆኑ በጥናትና ምርምር ሥራዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ቦርዱ አሳሰበ።

ዩኒቨርሲቲዉ “ምርምር ለዘላቂ ልማት” በሚል መሪ ቃል ስምንተኛዉን አገር አቀፍ የጥናትና ምርምር አውደ ጥናት በሶዶ በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ዳጋቶ ኩምቤ አውደ ጥናቱን ሲከፍቱ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲዉ የሚያከናውናቸውን ተግባራት ከአገራዊ የልማት ሥራዎች ጋር ማቆራኘት ይጠበቅበታል።

በተለይም በትምህርት ጥራት፣ በግብርና፣ በማህበራዊና ዘርፎች የሚካሄዱ ምርምሮች ማህበረሰብ ተኮርና ዘላቂ መሆን አለባቸው ብለዋል።

በዚህም ዩኒቨርሲቲው ለኣካበቢው ኅብረተሰብ አያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ ማሳደግ እንደሚጠበቅበት አመልክተዋል።

መንግሥት በአገራዊ ጉዳዮችና በልማት ሥራዎች ላይ የምሁራን ተሳትፎ ለማሳደግ የሰጠው ትኩረት በተግባር  እንዲታገዝም ጠይቀዋል።

የአገሪቱን የተፈጥሮና ባህላዊ ሀብቶች ዘለቄታዊ ጥቅም እንዲሰጡ ለማድረግ ምክረ ሐሳብ በማቅረብ መደገፍ  እንዳለባቸውም ምከትል ሰብሳቢው ጠቁመዋል።

የዩኒቨርሲቲዉ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የሚያካሂዳቸው ጥናቶችና ምርምሮች ችግር ፈቺና ውጤታማ ለማድረግ  እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በአውደ ጥናቱ የሚቀርቡ ሥራዎች የአገርን ልማት በዘላቂ መሰረት ላይ እንዲቆም ተሳታፊዎች ገንቢ አስተያየት በመስጠት እንዲያዳብሯቸው አሳስበዋል።

በዳዉሮና በወላይታ ዞኖች በከፈታቸው በስድስት የምርምር ማዕከላት ከ140 በላይ የምርምር ሥራዎች እያከናወነ መሆኑን የዩኒቨርሲቲዉ የምርምርና ማህበረሰብ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር መስፍን ቢቢሶ ተናግረዋል፡፡

በዋናነትም በግብርናዉ ዘርፍ በአጭር ጊዜ የሚደርሱና የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለሚያረጋግጡ ዝርያዎች ትኩረት መሰጠቱን  አስታውቀዋል።

ለምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ሥራዎች ማስፈጸሚያ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ መመደቡንም አስታውቀዋል።

በማዕከላቱ ከአውሮፓና ከእስያ አገሮች የተወሰዱ የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራዎች እየተተገበሩ መሆኑንም  ዶክተር መስፍን ገልጸዋል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው አውደ ጥናት 75 የጥናትና ምርምር ሥራዎች ይቀርባሉ።