በአገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን እናቶች ለሰላምና እርቅ መስራት እንደሚገባቸው ተገለፀ

94

ግንቦት 16/2011 በኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን የሴቶች ሚና የጎላ በመሆኑ እናቶች ለሰላምና እርቅ መስራት እንደሚገባቸው ተገለፀ።

የሰላም ሚኒስትር ከኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማህበር ጋር በትብብር ባዘጋጁት መድረክ ሴቶች በማህበረሰቡ ውስጥ ያላቸው ተቀባይነት ከፍተኛ በመሆኑ ለአገሪቱ ሰላም ከመቼውም ጊዜ በላይ መስራት እንደሚገባቸው ተጠቁሟል።

ዛሬ የተዘጋጀው መድረክ፤ የተለያየ አቋም የሚያራምዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከክልሎች የተወጣጡ ወጣቶች፣ ጦማሪያን እና የመብት ተሟጋቾችን በማሰባሰብበ በእናቶች አማካኝነት የሠላም ጥሪ ለማቅረብ ያለመ ነው።

በመድረኩ የእናቶች ከቀዬአቸው መፈናቀል በአገር ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ የሚፈጥር በመሆኑ እናቶች ለሠላምና እርቅ መስራት እንዳለባቸው ተነግሯል። 

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው በመድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ለአገር ልማትና እድገት ሰላም ከምንም ነገር በላይ የገዘፈ ዋጋ እንዳለው አብራርተዋል፡፡

ከግለሰብ የነገ የማደግና የመለወጥ ህልም ጀምሮ እስከ አገር ድረስ ሰላም ከደፈረሰ ምንም አይነት ራእይና ተስፋዎችን ማሳካት የማይቻል በመሆኑ ሰላም ይሰፍን ዘንድ ሁሉም ለሰላም ዘብ እንዲቆም ጠይቀዋል።

በተለይም ሴቶች በሰላም እጦት ዋነኛ ተጠቂ በመሆናቸው ሴቶች በማህበረሰቡ ውስጥ ያላቸውን ከፍተኛ ተቀባይነት ተጠቅመው ለአገሪቱ ሰላም መስራት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

የሴቶችና ህጻናት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ስመኝ ውቤ ''ሴቶች ሰላምን ሊጠብቁት ይገባል'' ብለዋል። ለሰላም መናጋት ዋነኛ ምክንያት ድህነት በመሆኑ ድህነትን ለማጥፋት ዜጎች ወደ ስራ እንዲሰማሩ ማድረግ የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማኅበር ፕሬዚዳንት ወይዘሮ እንግዳዬ እሸቴ በበኩላቸው፤ ''ሴቶች ባሉበት ሆነው ሰላምን ለማስጠበቅ ቢሰሩ ሰላምን ለማደፍረስ የሚሮጥ የትኛውም ኃይል ሀሳቡን ማሳካት አይችልም'' ብለዋል።

በአገራዊ መድረኩ የተለያየ አቋም የሚያራምዱ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ አክቲቪስቶችና እና ጦማሪያንን በማቀራረብ በአገር ሰላምና እርቅ ለማምጣት እናቶች ጥሪ ያደረጉበት መሆኑን ገልፀዋል።

በመድረኩ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና አባገዳዎችን ጨምሮ የሠላም አምባሳደር እናቶች እና ከሁሉም ክልሎች የተወጣጡ ሴቶች ተሳትፈዋል።

የሠላም አምባሳደር እናቶች ከወራት በፊት ‘የሚስተዋለው የእርስ በርስ ግድያ፣ ግጭትና መፈናቀል አሰጋን፣ አስጨነቀን’ በማለት ሠላም እንዲሰፍንና የዴሞክራሲ ጅማሮው እንዳይደናቀፍ ለመማፀን በተለያዩ ክልሎች ተንቀሳቅሰው ጥሪ ማድረጋቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም