ዘጠኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች ‘ብሔራዊ ግንባር’ ሊፈጥሩ ነው

2371

ግንቦት 16/2011 ሁለት አገራዊና ሰባት ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብሔራዊ ግንባር ሊፈጥሩ ነው።

የሚመሰረተው ብሄራዊ ግንባር የኢትዮጵያ አንድነት ብሔራዊ ግንባር የተሰኘ መጠሪያ እንደሚኖረው ተጠቁሟል።

የግንባሩ ምስረታ አስተባባሪ ኮሚቴ ጸሃፊ አቶ አንዷለም ጥላሁን ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ግንባሩን መመስረት ያስፈለገው በዓላማ ከሚመሳሰሉ ፓርቲዎች ጋራ ጥምረት በመፍጠር ለህዝብ ጠንካራ አማራጭ ሆኖ ለመቅረብ ነው።

ግንባር ለመመስረት የተስማሙ ፓርቲዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ኮንግረስ፣ የኢትዮጵያ ህብረ ህዝብ ብሔራዊ ንቅናቄ፣ የአገው ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የጋምቤላ  ህዝቦች ነጻነት ንቅናቄ፣ የደቡብ  ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ህብረት፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኮንግረስ፣ የጋምቤላ ህዝብ ፍትህ፣ ሰላምና ልማት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣ የሼኮና አካባቢው ዴሞክራሲያዊ ድርጅትና የአርጎባ ብሔረሰብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ፓርቲዎቹ ነገ የስምምነት ፊርማ የሚያደርጉ ሲሆን፤ በአጭር ጊዜ ምስረታ በማካሄ ወደ ስራ እንደሚገቡ ተናግረዋል።

ግንባር ለመፍጠር ከተስማሙት ዘጠኝ ፓርቲዎች በተጨማሪ ሌሎችም ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑን አቶ አንዷለም ጠቁመዋል።