የኢትዮጵያ ቅርሶችን ለዓለም ለማስተዋወቅ የጋራ እሴቶችን የሚያንጸባርቅ ብሄራዊ ሙዚዬም መገንባት ይገባል ተባለ

108

ግንቦት 16/2011የኢትዮጵያ ቅርሶችን ለዓለም ለማስተዋወቅ በቅድሚያ የጋራ አገራዊ እሴቶችን የሚያንጸባርቅ ብሄራዊ ሙዚዬም መገንባት እንደሚገባ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ሙዚዬም አስተባባሪ ፕሮፈሰር አህመድ ዘካሪያ ገለፁ። 
ኢትዮጵያን ጨምሮ መላው አፍሪካዊያንን የሚገልፅ "የአፍሪካ ሙዚዬም" በአልጀሪያ ለመገንባት እንቅስቃሴ ተጀምሯል።

በዚህ አፍሪካዊ ሙዚዬም ውስጥ የኢትዮጵያን ማንነት በአግባቡ የሚወክል ቅርስ ማቅረብ እንደሚጠበቅ ፕሮፌሰር አህመድ ለኢዜአ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ "ምን ትመስላለች" የሚለውን ስዕል ለዓለም ለማስተዋወቅ ህዝቦቿ በጋራ የተስማሙበት ብሄራዊ ሙዚዬም መገንባት ግድ እንደሚል ነው ፕሮፌሰሩ የገለፁት።

የሁሉንም አካባቢ ማኅበረሰቦች "እኔን ይወክለኛል" የሚሉትን ቅርስ ራሳቸው እንዲያቀርቡ በመፍቀድ ግዙፍ ብሄራዊ ሙዚዬም መገንባት እንደሚቻል ጠቁመዋል።

"በአንድ ብሄራዊ ሙዚዬም ሁሉንም ቅርሶች ማጨቅ ተገቢ አይደለም" ያሉት ፕሮፌሰር አህመድ፤ በተማከለ አስተዳደር የሚመሩ ብሄራዊ ሙዚዬሞችን በተለያዩ አካባቢዎች በመገንባት የተሻለ አማራጭ መሆኑንም ይጠቁማሉ።

የአካባቢው ማኅበረሰብ የተስማማበትን ቅርስ እንዲያቀርብ በመፍቀድ ኢትዮጵያን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማስተዋወቅ ይገባል ነው ያሉት።

ለዚህ ደግሞ ህዝቡንየሚወክሉ ቅርሶችን መንግስት ጣልቃ ገብቶ ከመምረጥ  ለቅርሱ ባለቤት እድሉን መስጠት እንደሚገባ ገልጸዋል።

ይህ ካልሆን ግን በአልጀሪያ ሊገነባ ለታሰበው የአፍሪካ ሙዚዬም ኢትዮጵያ የምትወከልበትን ቅርስ ለማቅረብ ይቸግራል ብለዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም የተገነባው ሙዚዬም ኢትዮጵያን ምን እንደምትመስል ለጎብኝዎች ያሳያል።

በመሆኑም ከዚህ ልምድ በመውሰን መንግስት ግዙፍ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሙዚዬም ገንብቶ የሀገሪቱን ገፅታ ማሳየት እንዳለበት ገልጸዋል።

ይህ ካልሆነ ግን ለአንድ ዜጋ የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ቅርስ፣ ገፅታና ነባራዊ ሁኔታ ለማስረዳት ከባድ ፈተና ይሆንብናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም