የኢንቨስትመንት አገልግሎት አቅርቦትን ያሻሽላሉ የተባሉ የኦንላይን አገልግሎት ቴክኖሊጂዎች ይፋ ሆኑ

88

ግንቦት 16/2011 የኢንቨስትመንት አገልግሎትን ቀልጣፋ እና ውጤታማ ማድረግ አላማ ያደረጉ የኦንላይን አገልግሎት ቴክኖሊጂዎች ዛሬ ይፋ ሆነዋል። 
የኦንላይን ኢንቨስትመንት አገልግሎት (online investement serivce platform) እንዲሁም የቻይና ባለሀብቶችን ተደራሽ የሚያደርግ ዌብ ፖርታል ዛሬ ይፋ የሆኑት የኦንላይን አገልግሎት ቴክኖሎጂዎች ናቸው።

የኦንላይን አገልግሎት ቴክኖሎጂዎቹን ይፋ የማድረግ ስነ ስርዓት ዛሬ የተካሄደ ሲሆን ቴክኖሊጂዎቹ ከዛሬ ጀምሮ ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።

የኦንላይን ኢንቨስትመንት አገልግሎት እንዲሁም ዌብ ፖርታሉን የገነቡት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ የዓለም ባንክ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን እና የዓለም የንግድ ተቋም በጋራ በመሆን ነው።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር አቶ አበበ አበባየሁ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ኮሚሽኑ ለውጭ ባለሀብቶች የሚሰጠውን አገልግሎት ይበልጥ ለማሻሻል ቀልጣፋ እና ውጤታማ አሰራሮችን በመዘርጋት ኢንቨስትመንትን ለማስፋት ጥረት እያደረገ ይገኛል።

ዛሬ ይፋ የተደረጉት የኦንላይን አገልግሎት ቴክኖሎጂዎች የዚሁ ጥረት አካል እንደሆኑም አንስተዋል።

የኦንላይን ኢንቨስትመንት አገልግሎት የውጭ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ምዝገባና የፈቃድ አሰጣጥ አገልግሎትን በኤሌትሮኒክስ ዘዴ ማግኘት የሚያስችላቸው እንደሆነ ተናግረዋል።

ባለሀብቶች ከዚህ በፊት የኢንቨስትመንት ምዝገባና የፈቃድ አገልግሎት ለማግኘት የተለያዩ ሰነዶችን ወደ ኢትዮጵያ ይዘው መምጣት የሚጠበቅባቸው እንደነበር አስታውሰው አዲሱ ቴክኖሎጂ ባሉበት ሆነው አገልግሎቱን እንዲያገኙ በማስቻል ጊዜና ወጪያቸውን እንደሚቆጥብ አመልክተዋል።

በኦንላይን አገልግሎቱ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ማግኘት፣ ማደስ፣ ማሻሻያ ማድረግና ማስፋት፣ ማሰረዝ እና ማስቀየር የሚያስችላቸውን አገልግሎት በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ ማግኘት እንደሚችሉም ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ማበረታቻ ጥያቄዎችን ኦንላይን ማቅረብ እንደሚችሉም አመልክተዋል።

የቻይና የዌብ ፖርታል የተዘጋጀው የኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ የኢንቨስትመንት አጋር የሆነቸው ቻይና ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ዙሪያ የሚፈልጉትን መረጃ ባለቡት ቦታ ሆነው እንዲያገኙ ለማድረግ ታስቦ እንደሆነ አቶ አበበ ተናግረዋል።

''የዌብ ፖርታሉ በአንግሊዘኛና በቻይና ማንደሪን ቋንቋ የተዘጋጀ ሲሆን የቻይና ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ስላሉ የኢንቨስትመንት እድሎችና አማራጮች፣ ህጎች፣ ማበረታቻዎች እና ሌሎች ተያያዥ መረጃዎችን ማግኘት ያስችላቸዋል'' ብለዋል።

የኦንላይን ኢንቨስትመንት አገልግሎት ለማዘጋጀት አንድ ዓመት ከስድስት ወር እንዲሁም የዌብ ፖርታሉን ለማዘጋጀት የስድስት ወር ጊዜ መውሰዱንና ለቴክኖሊጂዎቹ የወጣው ወጪ በልማት አጋሮች እንደተሸፈነም አመልክተዋል።

በዓለም ባንክ የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን ተወካይ ሚስተር ሄይንዝ-ዊለሄልም ስትሩቤንሆፍ በበኩላቸው ዛሬ ይፋ የሆኑት ቴክኖሎጂዎች ኢንቨስትመንት ኮሚሸን አገልግሎቱን ዘመናዊ የማድረግ ጥረቱ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢንቨሰትመንት አገልግሎቱን ቀልጣፋ እንዳይሆን ያደረጉ የአሰራር ችግሮችን መፍታት እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ በተለይም የኢንቨስትመንት ህጎችን ለማሻሻል ትኩረት መሰጠት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የእንግሊዝ ዓለም አቀፍ የልማት ዲፓርትመንት (ዲ.ኤፍ.አይ.ዲ) ተወካይ ሚስ ጌል ዋራንደር ኮሚሽኑ የጀመረው ራሱን የማዘመን ስራ መልካም የሚባል እንደሆነ ተናግረዋል።

የአገልግሎት ስርአቱን ለማቀላጠፍ ለባለሙያዎች ድጋፍ ማደረግ እንዳለበት ጠቁመዋል።

ኮሚሽኑ ከባለሀብቶች ጋር በመወያየትና ጥናት በማድረግ አዳዲስ የኢንቨስትመንት መዳረሻዎችን በማስፋት የኢንቨትመንት ብዝሃነት እንዲኖርም መስራት እንዳለበትም ጠቅሰው ለኢንቨስትመንት ኮሚሽን ዲኤፍአይዲ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ የኢኮኖሚና የንግድ አማካሪ አታሼ ሚስተር ዣንግ ዩ ዛሬ ይፋ የሆኑት ቴክኖሊጂዎች የአሰራር ሂደቶችን በማዘመን የቻይና ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ይበልጥ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ እንደሚያበረታታ አመልክተዋል።

በተለይም የዌብ ፖርታሉ ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ ያሉ የቻይና ኩባንያዎችን መረጃ የያዘ በመሆኑ ለአዲስ ባለሀብቶች መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥርም ገልጸዋል።

የኢንቨስትመንት ፈቃድ ክፍያ ኤሌትሮኒክስ መንገድ እንዲከፍሉ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑና አገልግሎቶቹ ለአደጋ እንዳይጋለጡ የተለያዩ የደህንነትና የጥበቃ ማሻሻያ ስራ እንደሚሰራ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ኢንቨሰትመንት ኮሚሽን የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት ዘርፍ በቴክኖሎጂ በመታገዝ የበለጠ ለማጎልበት የሚያስችል “IGuide” የተሰኘ የኦንላይን ድረ-ገጽ ቴክኖሎጂ በታህሳስ ወር 2011 ዓ.ም ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም