በሰቃ ከስጋት ወደ ልማት

218

ገብረህይወት ካህሳይ /ከኢዜአ/

የበሰቃ ሐይቅ ሲነሳ መተሀራ ከተማ አብሮ መነሳቱ ግድ ይላል። ምክንያቱም ሐይቁ እየተስፋፋና ወደ ከተማዋ እየተጠጋ በመምጣቱ በነዋሪዎች ዘንድ የመጥለቅለቅ ስጋት ከፈጠረ ቆይቷል።

ከስጋት በዘለለ በፍጥነት እየተስፋፋ በመምጣቱ ከ2004 ዓ.ም ወዲህ 1ሺህ 278 ሔክታር መሬት በመሸፈን የወጣቶች ማእከል፣ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ጤና ጥበቃ ፅህፈት ቤት፣ የከብት ማድለቢያዎች፣ የመንግስትና የግል መኖሪያ ቤቶች በማፈራረስ በርካቶችን ማፈናቀሉን የመተሀራ ከተማ አስተዳደር የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያ አቶ ገዛሊ ሀሰን ያስረዳሉ።

የሀይቁ የውሃ መጠን እየጨመረ በመምጣቱ የተሻለ አማራጭ ተደርጎ የተወሰደው የማስተንፈሻ ቦይ በመቅደድ እየተመጠነ ወደ አዋሽ ወንዝ እንዲለቀቅ ማድረግ ነበር።

ይህም ቢሆን በታችኛውና በመካከለኛው አዋሽ የልማት ተቋማትና በአፋር ክልል ነዋሪዎች ዘንድ ቅሬታ ማስከተሉ አልቀረም። ምክንያቱ ደግሞ የበሰቃ ሀይቅ ውሃ አሲዳማ ስለሆነ የአዋሽ ወንዝን ሊበክለው ይችላል የሚል ስጋት በማሳደሩ ነው።

የወረር ግብርና ምርምር ማእከልና የአዋሽ ተፋሰስ ባለስልጣን የበሰቃ ሃይቅ ውሃ በአዋሽ ወንዝ ላይ የሚያሳድረውን ተፅእኖ ለማለየት በዓመት ለአራት ጊዜ ናሙና በመውሰድ ጥናቶች ሲያካሔዱ ቆይተዋል።

በወረር ግብርና ምርምር ማእከል የዘርፉ ተመራማሪ አቶ አሸናፊ ወርቁ እንደገለፁት የበሰቃ ሀይቅ ውሃ የጥራት መጠኑ እያደገ መምጣቱንና በሒደት ለመስኖ ልማት መዋል እንደሚችል በጥናት መረጋገጡን አስረድተዋል።

ከአዲስ አበባ እስከ ታችኛው አዋሽ አፍአምቦ ድረስ በዓመት 4 ጊዜ የአዋሽ ወንዝ የውሃ ጥራት ናሙና እንደሚወሰድ ተመራማሪው ገልፀው የበሰቃ ሀይቅ የውሃው የጥራት መጠን ከ7 ነጥብ 4 ዴሲ ሳይመን ወደ  3ነጥብ 2 ዴሲ ሳይመን በመቀነስ ጥሩ የጥራት መሻሻል እያሳየ መሆኑን ተመራማሪው ይገልፃሉ።

የአዋሽ ተፋሰስ ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ አቶ አበጀ መንገሻ በበኩላቸው ከሀይቁ እየተመጠነ ወደ አዋሽ የሚለቀቀው ውሃ የሚያስከትለው ጉዳት የለም።

”እንዲያውም የሃይቁ ውሃ በየጊዜው ጥራቱ እየተሻሻለ በመምጣቱ ለመስኖ ልማት አገልግሎት የሚውልበት አማራጭ እየተፈለገ በመሆኑ ከአሁን በኋላ የበሰቃ ሀይቅ በረከት እንጂ ስጋት ሆኖ አይቀጥልም ” በማለት አስምረውበታል።

የመተሀራ ከተማ ነዋሪዎችም በበሰቃ ሐይቅ ላይ አንፃራዊ መሻሻል መመልከታቸውን ይመሰክራሉ። በመተሀራ ከተማ 02 ቀበሌ ነዋሪ አቶ ውብሸት መስፍን በሰጡት አስተያየት በአሁኑ ወቅት በመንግስት እገዛ ነዋሪው ከበሰቃ ወንዝ ስጋት እፎይታ አግኝቷል።

ሐይቁ መተንፈሻ ስለተሰራለት ከክረምት በስተቀር በበጋ ወራት የሚያሰጋ ነገር አለመኖሩን፤ እንዲያውም ቀጤማ ማብቀል መጀመሩን፣ ዓሳና አዞ በስፋት መራባት መጀመራቸውን አቶ ውብሸት ይናገራሉ።

የበሰቃ ሀይቅ በአግባቡ ከለማ ደግሞ እንደ ሀዋሳና ባህርዳር መተሃራን ሳቢ የመዝናኛ ከተማ ማድረግ የማይቻልበት ምክንያት የለም የሚል ተስፋ አላቸው።

የበሰቃ ሐይቅ እየተመጠነ ወደ አዋሽ ወንዝ መለቀቁና በሌሎች ላይ የጎንዮሽ ጉዳት እንደማያስከትል መረጋገጡ የከተማው ከንቲባ ወይዘሮ ሃልኮ ፈንታሌን በእጅጉ አስደስቷል።

ምክንያቱ ደግሞ የበሰቃ ሀይቅ በ1966 ዓም በትንሽ ቦታ መፍለቅ እንደጀመረና ባለፉት 45 ዓመታት በፍጥነት እየተስፋፋ መጥቶ በነዋሪዎቹ ዘንድ የመተሀራ ከተማን ሊያጥለቀልቃት ይችላል የሚል ስጋት አሳድሮ ለቆየው ህዝብ እፎይታ መሆኑን ጠንቅቀው ስለሚረዱ ነው። 

”የበሰቃ ሀይቅ በርካቶችን ያፈናቀለና ወደ ከተማዋ በመጠጋት ስጋት ፈጥሮ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ወደ አዋሽ ወንዝ በማስተንፈስ ህዝቡ እፎይታ ማግኘቱን ስመለከት ልዩ ደስታ ይሰማኛል” ይላሉ።

በአካባቢው ለ600 ሰዎች የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታና ካርታና ፕላን ተሰጥቶ እንደነበር በማስታወስ በሀይቁ መስፋፋት ምክንያት አካባቢው በውሃ በመጠቃቱ ዕቅዱ መስተጓጎሉን ከንቲባዋ ተናግረዋል።

በበሰቃ ወንዝ ይጠቃል ተብሎ ይሰጋ የነበረው ቀጠና 6 በተባለው አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎች ከቦታው ለማስነሳት የነበረው እቅድም አሁን በተፈጠረው የሃይቁ አንፃራዊ መቀነስ ምክንያት ባሉበት እንዲቆዩና ተረጋግተው መደበኛ ኑሮአቸውን እንዲመሩ ተደርጓል።

ሀይቁ በአሁኑ ወቅት ከስጋት ተላቆ የከተማዋ ውበትና የልማት ምንጭ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ የገለፁት የከተማዋ ከንቲባ፤ ባለሃብቶች በሀይቁ ዙሪያ የመዝናኛ ማእከላትን በመገንባት ለቱሪዝም እድገት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

እንደ አለመታደል ሆኖ ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት አልበቃም እንጂ በበሰቃ ሀይቅ ዳርቻ በዓይነቱ ልዩ የሆነ የመዝናኛ ስፍራ በ80 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ተገንብቶ ነበር።

በልዩ የኪነ ህንፃ ጥበብ እንደተገነባ የሚነገርለት ልዩ የመዝናኛ ስፍራ አገልግሎት መስጠት ሳይጀምር ለ8 ዓመታት ባለቤት አልባ ሆኖ በመቀመጡ አገልግሎት መስጠት ሳይጀምር መልሶ እየፈረሰ ነው።

ከመተሀራ ከተማ በ3 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በ143 ሔክታር መሬት  ተከልሎ የተገነባው ልዩ የመዝናኛ ስፍራ ከሩቁ  አሸብርቆ የሚታይ ቢሆንም የተሟላ መረጃ የሚሰጥህ ውስጥ አዋቂ ማግኘት ግን በእጅጉ አስቸጋሪ ነው።

ከርቀት ምንድን ነው ብለህ ብትጠይቅ በውጭ አገር ሰዎች የተገነባ ልዩ የመዝናኛ ስፍራ ነው ሲባል የሰማ እንጂ በእርግጠኝነት ዝርዝር መረጃ ያለው የለም።

ስለሁኔታው ለማወቅ ጉጉት ያደረበት የኢዜአ የጋዜጠኞች ቡድን ከፈንታሌ ወረዳ ኢንቨስትመንትና ከወረዳው የኮሙዩኒኬሽን ፅህፈት ቤት ሁለት ባለሙያዎችን በመያዝ ወደ ቦታው ያቀና ሲሆን ግንባታው የሚደነቅ ብክነቱ ግን የሚያሳዝን ሆኖ አግኝቶታል።

 ወደቦታው ለመግባት ሜዳ ሜዳውን እየመረጡና ከፕሮሶፒስ እሾሃማ መጤ አረም ጋር እየታገሉ መጓዝ እንጂ መኪና ሲመላለስበት የነበረው የገጠር መንገድ አገልግሎት ሳይሰጥ ረጅም ጊዜ ስለሆነው ተመልሶ ጠፍቷል።

በቦታው በበሰቃ ሀይቅ ዳርቻ እየዋኙ ከሚጫወቱ ጥቂት የአርብቶ አደር ህፃናት ልጆች በስተቀር አንድም የጥበቃ ሰራተኛ በስፍራው አልነበረም።

የፈንታሌ ወረዳ ኢንቨስትመንት ፅህፈት ቤት ባለሙያ አቶ ከማል ዑመር እንደሚሉት ግንባታው በ80 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጪ  ከ1999 ዓ.ም እስከ 2003 ዓ.ም በነበረው ጊዜ ውስጥ የተካሄደ ሲሆን ባለቤቱም ሶል ጆኦት ሳዑዲ አሜሪካን ኢንቨስትመንት ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባኒያ በሚል ስያሜ የተመዘገበ ነው።

የሳዑዲ አረቢያ ተወላጅ የሆኑት የኩባኒያው ባለቤት በ2003 ዓ. ም የበሰቃ ሀይቅ የውሃ መጠኑ ጨምሮ ወደ መዝናኛ ስፍራው በመግባት በግንባታው ላይ ጉዳት በማድረሱ ተበሳጭተው አካባቢውን ለቀው በመሄዳቸው ግንባታው ሙሉ በሙሉ ሳይጠናቀቅና አገልግሎት መስጠት ሳይጀምር መቅረቱን ባለሙያው አብራርተዋል።

በጊዜ ሒደት ባለሃብቱ እዛው አገራቸው ላይ እንደሞቱ የተሰማ ሲሆን ህጋዊ ወራሾች የሆኑ ቤተሰቦቻቸው ስራውን ለማስቀጠል  ፍላጎት እንዳላቸው ከሶስት ወር በፊት ለመንግስት አሳውቀው እንደተፈቀደላችው አቶ ከማል አስረድተዋል።

ግንባታው ከመቋረጡ በፊት አርብቶ አደሮችን ጨምሮ 300 ለሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች የስራ እድል የፈጠረ ነበር።

ወጣቱ ዓሳ አጥማጅ ዴቪድ ብርሃኑ  በመተሀራ ከተማ ቀበሌ 01 ተወልዶ ያደገ ሲሆን በመዝናኛ ስፍራው የሚገኘው አንዱን ማማ መኖሪያው አድርጎ እየተጠቀመበት  ዓመታትን አስቆጥሯል።

ወጣቱ ወደ ከተማ የሚወጣው ያጠመደውን የዓሳ ምርት  ለመሸጥ እንጂ ውሎ አዳሩ በመዝናኛ ስፍራው ውስጥ ነው ።

”ባለሃብቱ ጥሩ ሰው ነበሩ። ለበርካታ ወጣት አርብቶ አደሮች የስራ እድል በመፍጠር ተጠቃሚ አድርገው ነበር። አካባቢውን ለቀው ከሔዱ በኋላ ብዙ ንብረት ተዘርፏል። ግንባታው አገልግሎት ሳይጀምር መልሶ እየፈረሰ በመሆኑ  ዘላቂ መፍትሄ ቢበጅለት መልካም ነው ” የሚል አስተያየትም ሰጥቷል።

አሁን የበሰቃ ሐይቅ ቀን ወጥቶለታል። ከስጋትነት ወደ ልማታዊ አማራጭነት ተሸጋግሯል። የከተማዋ ከንቲባም በሀይቁ ዙሪያ መዋእለ ንዋያቸውን ለሚያፈሱ ባለሃብቶች መልካም አቀባበል ለማድረግ ዝግጁ እንደሆኑ አረጋግጠዋል።

በድንቅና ልዩ የመዝናኛ ስፍራ የተሟሸው በሰቃ የመተሀራ ከተማን ተመራጭ የጎብኚዎች መዳረሻ ለማድረግ በሚደረገው ርብርብ የአዋሽ ተፋሰስ ባለስልጣን ተገቢውን እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑ ደግሞ ተጨማሪ አቅም ነው።

መልካም ጊዜ ለመተሀራ ከተማ ከበሰቃ ሐይቅ ጋር!!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም