በኢትዮጵያ በዚህ ዓመት በበልግ እርሻ ከአንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ በተለያዩ ሰብሎች ተሸፍኗል

82

አዲስ አበባ ግንቦት 16/2011 በኢትዮጵያ በዚህ ዓመት በበልግ እርሻ ከአንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ በተለያዩ ሰብሎች መሸፈኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።


በመላው ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት ከታቀደው የበልግ እርሻ ልማት የመሬት ሽፋን ከ 1ነጥብ 94 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ሲሆን ከዚህ ውስጥ ወደ 26 ሚሊዮን ኩንታል ይገኛል ተብሎ ነው የሚጠበቀው።


እንደ አገር ከአጠቃላይ የአዝዕርት ሰብሎች ምርት ውሰጥ 11 በመቶ በምርት የደረጃ፣ በመሬት ሽፋን ደግሞ ወደ 5 ከመቶ የሚሸፍን በበልግ እርሻ ምርት ሲሆን የደቡብና የኦሮሚያ ክልሎች ሰፊውን የበልግ ሽፋን ይይዛሉ።


የግብርና ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ብርሃኑ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በበልግ እርሻ በሰብል ለመሸፈን ከታቀደው መሬት ውሰጥ 67 በመቶ በተለያዩ ሰብሎች ተሸፍኗል።

የእርሻ መሬቶቹ በበቆሎ፣ ገብስ፣ ስንዴ፣ ቦለቄ፣ ማሽላ በመሳሰሉት ሰብሎች የተሸፈኑ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ በሚይዘው የበቆሎ ሰብል 450 ሺህ ሄክታር መሬት ተሸፍኗል:;

ግብዓትን በተመለከተም ከ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮንሜትሪክ ቶን በላይ የአፈር ማዳበሪያ የቀረበ ሲሆን 1 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ ለበልግ እርሻ ስራ ጥቅም ላይ መዋሉን ተናግረዋል።
በመጀመሪያ የበልግ መግቢያ አካባቢ የዝናቡ ሁኔታ የተቆራረጠ በመሆኑ ለማካካስ እየተሰራ እንደሆነ የተናገሩት አቶ አለማየሁ እስከ ግንቦት 30 ድረስ የሚቀረውን የበልግ ስራ ለመሸፈን እንደሚሞከር ጠቁመዋል። 

የበልግ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች ላይ የዝናብ እጥረት የሚያጋጥማቸው አካባቢዎች በመሆኑ ቅድመ ጥንቃቄ እንዲደረግ የግንዛቤ ማስጫበጫ ለአርሶ አደሩ መደጠቱን ተናግረዋል።
የዝናብ እጥረት ሲያጋጥም ቶሎ የሚደርሱ ሰብሎች እንዲዘሩ የባለሙያ ምክር ለአርሶ አደሩ መሰጠቱንና የዝናብ ውሃን ማቆር ስራዎች ቀድሞውኑ እየተሰራበት የነበረ መሆኑን ጠቁመዋል።

በበልጉ አልፎ አልፎ የዝናብ ሁኔታ ከመዋዋዠቁ በስተቀር የከፋ ጉዳት እንዳላጋጠመም ገልጸዋል።
ደቡብ ወሎ፣ባሌ፣ቦረና፣ጉጂ፣ደቡብ ትግራይ ዞኖች በተወሰኑ ወረዳዎች የዝናብ መዋዠቅ ቢታይም የከፋ ጉዳት አለመድረሱን ተናግረዋል።
የዝናብ ውሃ እጥረት የሚታይባቸው አካባቢዎች ላይ ዉሃን የማሰባሰብ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ በዚህም የመተካት ሁኔታዎች ስላለ የከፋ ችግር እንደማያስከትል ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም