በክልሉ የአመራሩና ባለሙያው ክፍተት ለግብርናው ምርታማነት ማነቆ መሆኑ ተገለጸ

239

አሶሳ ግንቦት 15 / 2011 ዓ.ም.በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአመራሩ እና የባለሙያው የአገልጋይነትና ህዝባዊ ወገንተኝነት ማነስ የግብርናው ዘርፍ በሚፈለገው መጠን ምርታማነቱ እንዳያድግ ማነቆ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ዘጠነኛው የክልሉ ግብርና ልማት አካላት ግንኙነትና የእሴት ሰንሰለት የምክክር መድረክ ዛሬ በአሶሳ ከተማ ተጀምሯል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት በክልሉ አርሶ አደሩን ከዘልማድ የግብርና አሠራር በማላቀቅ በተከናወኑ ተግባራት የተገኙ ውጤቶች አሉ፡፡

የግብዓት አጠቃቀም መሻሻልና አልፎ አልፎ በተናጠልም ይሁን በተደራጀ መልኩ በትራክተር የማረስ ልምድ ብቅ እያለ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ሆኖም ውጤቱ በሚፈለገው ልክ እንዳልሆነ ያመለከቱት ርዕሰ መስተዳድሩ “የችግሩ ዋነኛ ምክንያቶች ደግሞ ለዘመናት ይዘን የዘለቅናቸው ጎታች አስተሳሰብና ጉልበት ጨራሽ የሥራ ልምዶች ናቸው” ብለዋል፡፡

ችግሮቹ በጥልቀት ሲታዩ ደግሞ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች እና አንዳንድ ፈጻሚ ባለሙያዎች ዘንድ የአገልጋይነትና ህዝባዊ ወገንተኝነት ማነስ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

ቅንጅታዊ አሠራር አለመዳበር፣ የህብረት ሥራ ማህበራት አቅም ውስንነት፣ ድጋፍና ክትትል አለመኖርና  ኪራይ ሰብሳቢነት ሌሎቹ የጠቀሷቸው ችግሮች ናቸው፡፡

እንደ ርዕሰ መስተዳድሩ ገለጻ ክልሉ ካለው የተፈጥሮ ሃብት ሲነጻጸር ለማመን በሚያስቸግር መልኩ አሁንም በከፋ ድህነት ውስጥ የሚገኙ አርሶ አደሮች ይገኛሉ፡፡

“ዘርፉን ለመለወጥ በእልህ እና በቁጭት ልንሠራ ይገባል “ብለዋል፡፡

የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሳ አህመድ በበኩላቸው በክልሉ ግብርናው የሥራ እድል በመፍጠርና ምጣኔ ሀብትን  በማሳደግ ረገድ የተጫወተው ሚና ዝቅተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

በምክክር መድረኩ ችግሮቹን የሚመለከቱ የመወያያ ሰነድ መዘጋጀቱን ጠቅሰው የመፍትሔ አቅጣጫዎች እንደሚጠበቁ አመልክተዋል፡፡

እስከ ነገ በሚቆየው መድረክ ከክልሉ ወረዳዎች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው፡፡