ከ60 ሺህ በላይ ሰዎች የሚካፈሉበት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በመጪው እሁድ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

109

አዲስ አበባ ግንቦት 15/2011 ከ60 ሺህ በላይ ሰዎች የሚካፈሉበት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በመጪው እሁድ ግንቦት 18 ቀን 2011 ዓ.ም እንደሚካሄድ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ገለጸ። 

የአካል ብቃት እንቅስቃሴው ''ዘረኝነት ይብቃ '' በሚል መሪ ሀሳብ እንደሚካሄድ ቢሮው አስታውቋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ  ኃላፊ አቶ ዮናስ አረጋይ እንዳሉት፤ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚካሄደው ተግባሩ ባህል እንዲሆን ከማድረግ ባለፈ እየተሰፋፋ የመጣውን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል ያግዛል።

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ በህብረተሰቡ ዘንድ አንድነት ለመፍጠርና ማህበራዊ ግንኙነትን ለማጠናከርም እንደሚያስችል ገልጸዋል።

የሰላም መስበኪያ የሆነው ስፖርት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እየታየ ያለውን የዘረኝነት አስተሳሰብ ለማክሰም የሚያስችሉ መልእክቶችን ለማስተላለፍ ጭምር የሚካሄድ መርሐ ግብር እንደሆነም ጠቁመዋል።

የስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ርስቱ ይርዳ በበኩላቸው ''ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የህብረተሰቡ የአኗኗር ሁኔታ እየተቀየረ በመምጣቱ የሰዎች የጤና ሁኔታ አደጋ እያጋጠመው ነው'' ብለዋል።

እንዲህ ዓይነት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ጤናማ ህብረተሰብ ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን የጥላቻ፣ የቂምና የበቀለኝነትን አስተሳሰብን ለማስወገድ በመንግስት ደረጃና በሐይማኖት አባቶች በኩል እየተሰራ ያለውን ስራ በስፖርቱ በኩል ለመድገም እንደሆነም አመልክተዋል።

በመጪው እሁድ ግንቦት 18 ቀን 2011 ዓ.ም በሚደረገው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ሁሉም ሰው ተሳታፊ እንዲሆን ጥሪ ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም