ኢትዮጵያ አዲስ ለተገኘችው ግዙፍ የህዋ አካል ስያሜ እንድታወጣ ዕድሉ ተሰጣት

75

አዲስ አበባ ግንቦት 15/2011ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የተገኘውን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ለተገኘችው አዲስ የህዋ አካል ስያሜ አሰጣጥ ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ ቀረበ።


የተገኘውን የህዋ አካልና ስያሜውን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ  ሶሳይቲና  የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዛሬ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን በላይ በዚሁ ግዜ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ላለፉት 15 ዓመታት በህዋ ሳይንስ ምርምር ላይ በርካታ  ስራዎችን ስታከናውን ቆይታለች።

በዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፔስ ሳይንስ ዘርፍ ተጠቃሽ ከሆኑ አገራት ተርታ ከመሆኗ ባሻገር በአፍሪካ ካሉትና በዘርፉ ከሚሰሩ ስድስት አገራት ውስጥ ቀዳሚውን ስፍራ  አንድትይዝም አድርጓታል።

በተለይም ዘርፉን የሚያግዙ ከ42 በላይ ጥናትና ምርምሮችን በማካሄድ ረገድ በስፔስ  ሳይንስ ላይ ያላትን ጉልህ ሚና በስፋት እያከናወነች መሆኑንም እንዲሁ።

በተጨማሪም አገሪቷ የራሷን የምርምር ማእከል በመክፈት ከምታከናውነው የምርምር  ስራዎች ባሻገር በዘርፉ የሚሰሩተተኪ ትውልድ በብቃት የማፍራት ስራዎችን እያከናወነችነው፤  ከምስራቅ  አፍሪካ አገራት ዜጎች እንዲመጡና ስልጠና እንዲያገኙ  ማድረጓም  ተመራጭ አድርጓታል ነው ያሉት።  

በነዚህና ሌሎች መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ያላት አስተዋጽኦን በመገንዘብ የህዋው  ዓለም  አቀፉ ህብረት(international astronomical union-IAU)እውቅና ከመስጠት ባሻገር አዲስ ለተገኘችዋ የህዋ አካል ስያሜ እንድታወጣ እድሉን  ሰጥቷታል  ብለዋል።

ስያሜው በሳይንሳዊ መለያው HD16175ተብሎ የሚታወቅ ኮከብና HD16175b  ተብላ  የምትታወቀዋ ፕላኔት የሚገኙበትን ስርዓት መሰየም እንደሆነ በመጠቆም።

ለዚህም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የተገኘውን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም  ለተገኘው  ግዙፍ የህዋ አካል ስያሜ በመስጠት ረገድ በስፋት እንዲሳተፉ ጥሪ አስተላልፈዋል።

ኮከቧ ከጸሃይ 1 ነጥብ 34 ጊዜ የምትገዝፍና ስፋቷም ከጸሃይ 1 ነጥብ 66 ጊዜ  ያህል  የምትበልጥ እንዲሁም ከሶስት እጥፍ በላይ ከጸሃይ በላይ የምታበራ መሆኗንም አብራርተዋል።

ፕላኔቷ በግዙፍነቷ ጁፒተር ከሚባለው ፕላኔትም ከ4 ነጥብ 8 ግዜ በላይ የምትበልጥ ሲሆን ሁለቱም ግዙፍ የህዋ አካላት በ196 የብርሃን ዓመት አካባቢ ከኛ ጸሃይ ርቀው በእኛው  ጋላክሲ  ውስጥ የሚገኙ ናቸውም ብለዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ኢትዮጵያ የምታወጣው ስያሜ ዝንተ አለም የሚቆይ  ከመሆኑም ባሻገር ለዚህ ግዙፍ የህዋ አካል ስያሜ  መመረጧም  ልዩ  ያደርጋታል  ሲሉም ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ዋና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ቤዛ ተስፋዬ  በበኩላቸው  አሰያየሙ በተቻለ መጠን ሰፊና ህዝባዊ ተሳትፎ እንዲኖረው የሚያስችል  አሰራር ይፈጠራል።

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ትምህርት ቤቶች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ  ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ምሁራን፣ ጋዜጠኞች፣ ሲቪክ ማህበራት፣ በግልና  በመንግስት  የሚሰሩ ሰራተኞች ፣የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች፣ እድሮች፣ የከተማና የገጠር ነዋሪዎች ፣የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ሌሎችም በስያሜው እንዲሳተፉና አስተዋጿቸውን እንዲያበረክቱ ጠይቀዋል።

የስያሜ ምርጫቸውን የሚያሳውቁበት አሰራርን በሚመለከት ቀላልና ምቹ  የሆኑ  አሰራሮችን ለመጠቀም በሚያስችል መልኩ እንዲከናወንና ስያሜው ምን  አይነት  ይዘት ሊኖረው  እንደሚገባም የሚያትት መረጃ  በቅርቡ ይፋ እንደሚሆን ነው ያብራሩት።

የስያሜ ሂደቱ በፈረንጆች አቆጣጠር እስከ ኖቬምበር 15 ቀን 2019 ድረስ  የሚከናወን  መሆኑን ጠቅሰው እድሉን ለመጠቀም ሰፊ ግዜ የተሰጠ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ዜጎች ለስያሜው  ከወዲሁ ዝግጅት እንዲያደርጉም አጽንኦት ሰጥተዋል።

በዘርፉ ከፍተኛ ጥናትና ምርምር ያካሂዳሉ ተብለው ከሚታመንባቸው ተተኪ ትውልድ መካከል ታዳጊ ሮቤል ባምላክ በተጋባዥ እንግድነት የተገኘ ሲሆን ስያሜ እንዲሰጥ በቀረበለት ጥያቄ መሰረትም ኢቴል የሚል ስያሜን  ለፕላንቷ የሰጠ ሲሆን ዩቶጵ ደግሞ ለኮከቧ የሰጣት ስያሜ ሆኗል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም