የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው

81

ግንቦት15/2011የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ምክር ቤት 4ኛ ዙር 6ኛ ዓመት 18ኛ መደበኛ ጉባኤውን ማካሄድ ጀመረ፡፡

ምክር ቤቱ በዛሬው ውሎው የ 2011 ዓ.ም የዘጠኝ ወር የሥራ አፈጻጸም ሪፖርትን እየገመገመ ነው፡፡

የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ኃይሉ ሚሰው በጉባኤው መክፈቻ ላይ እንዳሉት በሀገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ ሂደት ስኬታማ ለማድረግ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው።

በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት ሥራ አስፈጻሚዎች የህብረተሰቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት ጥረት ቢያደርጉም ፈጣን ምላሽ ከመስጠት አንጻር አሁንም ክፍተት መኖሩን ተናግረዋል፡፡

አመራሩና ባለሙያው ለውጡን የሚመጥን አገልግሎት ለህብረተሰቡ መስጠት እንዲችሉ ተገቢው ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ ተገቢ መሆኑንም አመልክተዋል።

አቶ ኃይሉ እንዳሉት በብሔረሰብ አስተዳደሩ የሰፈነው ሰላም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሕብረተሰቡን በባለቤትነት በማንቀሳቀስ መስራት ያስፈልጋል፡፡

ምክር ቤቱ በዛሬው ውሎው በ17ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ የተቀመጡትን የትኩረት አቅጣጫዎች መሰረት በማድረግ የተለያዩ የመንግስት ተቋማትን የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም አድምጦ እየገመገመ ነው፡፡

በሁለት ቀናት ቆይታውም የተቋማትን አፈጻጸም ከመገምገም ባለፈ ለቀጣይ አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በተጨማሪም የብሔረሰብ አስተዳደሩን የከፍተኛ ፍርድ ቤት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም እንዲሁም የውስጥና የውጭ የኦዲት ግኝት ሪፖርት አድምጦ እንደሚገመግም ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም