ኮሌጁ 750 ሺህ ብር ግምት ያላቸው የትምህርት መሳሪያዎችን በድጋፍ አገኘ

123

ግንቦት 15/2011 ሽሬ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ 750 ሺህ ብር ግምት ያላቸው የትምህርት መርጃ መሳሪያዎችን ድጋፍ አገኘ።
ድጋፉ ኮሌጁ በመጨው ዓመት ለሚጀምረው የመአድን ትምህርት አገልግሎት ጠቀሜታ እንዳለው ተመልክቷል።

ኮሌጁ አጋዥ የትምህርት መሳሪያዎችን በእርዳታ ያገኘው በካናዳ መንግስት ከሚታገዘው የስትሬንግዝን ቴክኒካል ኤንድ ቮኬሽናል ኢዱኬሽናል ሴንተር ፕሮጀክት ነው።

የኮሌጁ ዲን መምህር ፀጋይ ገብረሚካኤል ድጋፉን በተረከቡበት ውቅት እንዳሉት ኮሌጁ በመጨው ዓመት ለመጀመርያ ጊዜ በመአድን ዘርፍ በተለይ በወርቅ ምርት ላይ ያተኮረ የሙያ ትምህርት  መስጠት ይጀምራል።

የትምህርት መሳሪያዎቹ ድጋፍ ለትምህርቱ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው  "ትምህርቱ በዞኑ ያለውን የመአድን ክምችት በተለይ የደለል ወርቅ ምርት በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችሉ ባለሙያዎችን በደረጃ አንድና ሁለት ለማፍራት ፋይዳው የጎላ ነው" ብለዋል።

መምህር ጸጋይ እንዳሉት ኮሌጁ በመጪው አዲስ ዓመት ከ100 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ በዘርፉ ለማስልጠን ዕቅድ ይዟል።

በዞኑ በዘፈቀደ በባህላዊ መንገድ እየተመረተ ያለው የደለል ወርቅ ምርት ከፍተኛ ጉልበትና ድካም ከመጠየቁ ባለፈ ለብክነት፣ ለደን ውድመትና ለሰው ሞት እያጋለጠ መሆኑን የተናገሩት ዲኑ፣ ይህን ችግር ለመቅረፍ የሰለጠነ የሰው ኃይል እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

የስትሬንግዝን ቴክኒካል ኤንድ ቮኬሽናል ኢዱኬሽናል ሴንተር ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አለምሰገድ ወልደገሪማ የእርዳታ መሳሪያዎቹን ባስረከቡበት ወቅት እንዳሉት፣ የመሳሪያዎቹ እርዳታ የመአድን ዘርፉን በትምህርት ለማገዝ የሚያስችል ነው።

"ድጋፉ በሙከራ ደረጃ በትግራይ ክልል በአክሱምና ሽሬ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች ስልጠና ለመስጠት ያስችላል" ብለዋል።

አጋዥ የትምህርት መሳሪያዎቹ ከ750 ሺህ ብር በላይ ወጪ እንደተደረገባቸው የተናገሩት አስተባባሪው፣ ድጋፉ በባህላዊ መንገድ እየተመረተ ያለውን የደለል ወርቅ በዘመናዊ መሳርያ ታግዞ በብዛትና በጥራት ለማምረት ዕድል እንደሚሰጥም አመልክተዋል።

የትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን በደለል ወርቅ ክምችት የታወቀሲሆን ከእዚህ በዓመት በባህላዊ መንገድ ከሰባት ኩንታል በላይ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ እንደሚቀርብ ከዞኑ የመአድንና ኢነርጂ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም