በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስወገድ ድጋፍ ተጠየቀ

98

ግንቦት 14/2011 በደቡብ ክልል በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስወገድ የባለድርሻ አካላት ድጋፍ ተጠየቀ 

በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች መከላከልና ማስወገድ በሚቻልበት ዙሪያ የተዘጋጀ ክልል አቀፍ የንቅናቄ መድረክ በአርባ ምንጭ ከተማ ተካሄዷል

ባለድርሻ አካላት በተሳተፉበት በዚሁ መድረክ በክልሉ ሴቶች ፣ ህፃናትና ወጣቶች ቢሮ  የሴቶች ንቅናቀ ተሳትፎ ማስፋፊያ ዳይሬክቶሬት ባለሙያ አቶ ተስፋዬ ማሞ እንዳሉት የሴት ልጅ ግርዛት ፣ ያለዕድሜ ጋብቻ ፣ ድርብና  የውርስ ጋብቻ ያልተወገዱ ድርጊቶች ናቸው፡፡

የከንፈርና ጆሮ ትልተላ  እንዲሁም የልጃገረዶች ግርፋት ሌሎቹ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እንደሆኑ አመላክተዋል፡፡

በማህበረሰብ ውስጥ በግንዛቤ ክፍተት ሚዛናዊ ያልሆነ የሴቶችና የወንዶች ደረጃ እና ድህነት አባባሽ ምክንያቶች ናቸው ተብሏል፡፡

በዚህም የህብረተሰቡ ግማሽ አካል የሆኑ በርካታ ሴቶች የአእምሮ ፣ የአካልና የስነተዋልዶ ጤና ችግር ሰለባ ተጋላጭ ናቸው፡፡

የቢሮው ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ አፀደ አይዛ በበኩላቸው ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት በሁሉም ዘርፍ የሴቶችን ተሳትፎና ና ተጠቃሚነት ከማቀጨጩም ባሻገር የሀገር ልማት እንዳይፋጠን  አሉታዊ ጫና እንደሚያሳድር ገልጸዋል፡፡

"በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጸሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቀረት የግንዛቤና የህግ ማዕቀፍ ሥራዎች ቢሠሩም የተፈለገው ደረጃ ላይ አልተደረሰም" ብለዋል፡፡

በክልሉ በ2020 ዓ.ም. ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ከሚፈጸምባቸው ቀበሌዎች  አንድ ሦስተኛውን ነፃ ለማድረግ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት የባለድርሻ አካላት ድጋፍ ጠይቀዋል፡፡

ድርጊቱን ለመከላከል በተፈጠረው የግንዛቤ ሥራ ያለዕድሜ ጋብቻ ፣ከንፈር መተልተል፣ የሴቶች ግርፋትና ግርዛት ከቀድሞ እየተሻሻለ ማምጣቱን የተናገሩት ደግሞ የደቡብ ኦሞ ዞን ሴቶችና ህፃናት መምሪያ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ እቴቴ አያለው ናቸው ፡፡


እንዲሁም በአከባቢው  ሚንጊ ተብለው ሊጣሉ  የነበሩ ከ200 በላይ ህፃናት ማሳደግ መቻሉንና  ከንፈራቸውን የተተለተሉ ሴቶች በህክምና እርዳታ  እየተመለሰላቸው እንደሚገኝም ጠቁመዋል ፡፡

ችግሩን ለማስወገድ ከፍትህ አካላት ፣ ከኃይማኖት አባቶችና በዘርፉ ከተዋቀሩ አደረጃጀቶች ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡

ከሃላባ የመጡ የኃይማኖት አባት አባ ብርሃነ መስቀልተስፋዬ በሴቶች ላይ የሚደርሰው በደል ለማስቀረት  በሁሉም ማህበረሰብ ዘንድ ግንዛቤ ለመፍጠር መሠራት እንደሚገባ አመልክተዋል።

የሴቶች ፣ ህፃናትና ወጣቶች ቢሮ ከወርሊድ ቪዥን ጋር በመተባበር ትላንት ባዘጋጀው የአንድ ቀን የንቅናቄ መድረክ ከክልሉ ሁሉም ዞኖች የተወጣጡ የኃይማኖት አባቶች፣ የፍትህ እና  ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም