የወጣቶች ንቅናቄና ተሳትፏዊ መድረክ በሀዋሳ ከተማ ተጀመረ

79
ሃዋሳ ግንቦት 29/2010 የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል አቀፍ ስምንተኛው የወጣቶች ንቅናቄና ተሳትፏዊ መድረክ ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ተጀመረ፡፡ በመድረኩ መክፈቻ ስነስርዓት ወቅት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደሩ ተወካይ አቶ ኤልያስ ሽኩር እንዳሉት መንግስት የወጣቱን ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ችግሮች በመለየት ለመፍታት እየሰራ ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት የክልሉ መንግስት የወጣቱን ችግሮች ለመፍታት ባከናወነው ተግባር መካከለኛ ገቢ ያላቸውን ባለሀብት ወጣቶችን ማፍራት መቻሉን አመልክተዋል፡፡ "እያደገ ከመጣው የወጣቶች ቁጥርና ፍላጎት አንጻር ያልተመለሱ በርካታ ጥያቄዎች መኖራቸውን በመረዳትና ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በማስተባበር የወጣቱን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት እየሰራ ነው" ብለዋል፡፡ ከከተሞች ማደግና መስፋፋት እንዲሁም ከቴክኖሎጂ እድገት ጋር ተያይዞ የሀገሪቱን ባህል የሚጻረሩ መጤ ጎጂ ባህሎችና አደገኛ እጾች መስፋፋት ወጣቱ በዕውቀትና በክህሎት ታንጾ እንዳያድግ እንቅፋት እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡ ይህንን ችግር ለመከላከል በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ መሰረት መስቀሌ በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት በክልሉ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ "ወጣቱ በክልሉ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታዎች ላይ በንቃት እንዲሳተፍ ለማድረግ በየደረጃው የተለያዩ የወጣት አደረጃጀቶችን ማቋቋም ተችሏል" ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ እየተወሰዱ ያሉ የለውጥ እርምጃዎች በተሳካ ሁኔታ እንዲቀጥሉ ለማድረግ ወጣቱ ከምንግዜውም በላይ ከመንግስት ጎን በመቆም የሚጠበቅበትን መወጣት እንዳለበትም አመልክተዋል፡፡ "ወጣቱ የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ መሆኑን በመረዳት ጊዜውን፤ ዕውቀቱንና ጉልበቱን በመጠቀም በትምህርት ተቋማትና በወጣት አደረጃጀቶች መጤና ጎጂ የሆኑ የባህል ወረርሽኝ ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ውስጥ የራሱን ድርሻ ማበርከት አለበት" ብለዋል፡፡ ለሁለት ቀናት በሚቆየው መድረክ በክልሉ በሚገኙ ሰባት ዩኒቨርሲቲዎች የአደንዛዥ እጾችንና ሌሎች ጎጂ ድርጊቶች መከላከል ላይ ባጠኑት መሰረት በተዘጋጀ የወጣቶች ስብዕናን ግንባታ የአምስት ዓመት ስትራተጂካዊ እቅድ ላይ ውይይት ይደረጋል፡፡ ወጣቶቹ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጋር የውይይት መድረክ የሚኖራቸው ሲሆን በክልል ደረጃ ሞዴል የሆኑ ወጣቶችና አደረጃጀቶች ሽልማት እንደሚሰጥ በመድረኩ ተገልጿል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም