የብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸውን የእንስሳትና እፅዋት ዝርያዎችን ለመታደግ እየሰራ ነው

281

ግንቦት 14/ 2011 የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸውን የእንስሳትና እፅዋት ዝርያዎች ለመታደግ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ። 
ኢንስቲትዩቱ 18ኛውን ዓለም አቀፍ የብዝሃ ህይዎት ቀን ’’ብዝሃ ህይዎታችን ምግባችን፣ ጤናችን’’ በሚል መሪ ሃሳብ እያከበረ ይገኛል።

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ፈለቀ  ወልደየስ   በሰጡት መግለጫ ባለፉት 100 ዓመታት በኢትዮጵያ 90 በመቶ የሰብል ዝርያዎች እንዲሁም 50 በመቶ የእንስሳት ዝርያዎች በመጥፋታቸው አገር በቀል መድሃኒቶችን ማግኘት አልተቻለም።

እየተባባሰ ለማጣው ችግር እልባት ለማበጀት ኢንስቲትዩቱ ከተለያዩ የምርምር ተቋማት ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑም ታውቋል።በዚህም ለመጥፋት ተቃርበው የነበሩ ከ80 በላይ የሰብል ዝርያዎች ለአርሶ አደሩ በማከፋፈል የማራባት ስራ እየተከናወነ ይገኛል።

አገር በቀል የሰብል ዝርያዎችን በውጭ አገር የሰብል ዝርያዎች በመተካት ምርታማ መሆን ይቻላል የሚለውን የተዛባ አመለካከት ለማስትካከልም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።ለብዝሃ ህይወት መመናመን ምክንያት ከሆኑት መካከል መጤና ወራሪ የሆኑ ዝርያዎች እንደ እንቦጭና ሌሎችንም አረሞች ለማጥፋት ጥረት እየተደረገም ይገኛል ነው ያሉት።

እንደዋና ዳይሬክተሩገለፃበቀጣይብዝሃ ህይዎትን ለመጠበቅእንዲቻል ከአስፈፃሚ እሰከ ፈፃሚ አካላት አስተባብሮ ለመስራት ጠንካራ የአሰራር ስርዓት ተዘርግቷል።

ለውጭ አገር ምርምር የሚፈለጉ የሰብል ዝርያዎች ተለይተው በኢንስቲትዩቱ  እውቅና ተሰጥቷቸውእንድተላለፉእየተደረገ ሲሆን በሌሎች አገሮች የባለቤትነት ጥያቄ እንዳይነሳባቸው በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ብዝሀ  ህይዎት  በሁሉም እጅ ላይ የሚገኝ በመሆኑ እንዲጠበቁ በማድረግ ህብረተሰቡ የበኩሉን እንዲወጣም ጥሪያቸውን አስትላልፈዋል።

ኢንስቲትዩቱ እ.ኤ.አ በ1976 በኢትዮጵያና በጀርመን መንግስት መካከል በተደረገው የትብብር ስምምነት መሰረት የዕፅዋት ጀነቲክ ሀብት ማዕከል በሚል ለመጀመሪያ ጊዜ ተቋቋመ፡፡

እ.ኤ.አ በ2013 ደግሞ የዘለቄታዊ አጠቃቀምና የጀነቲክ ሀብት ፍትሀዊ ተጠቃሚነትንና የምርምር ስራዎችን በማካተት የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት በሚል እንዲቋቋም መደረጉን መረጃዎች ይጠቁማሉ።