የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተመራቂ የተማሪዎችን የስራ አለም ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ እየሰራ ነው

69

ግንቦት 14/ 2011የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎች በስራ አለም የሚኖራቸውን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ።
ዩኒቨርሲቲው ተመራቂ ተመራቂ ተማሪዎች ከቀጣሪ ድርጅቶች ጋር የሚተዋወቁበት የሁለት ቀናት  ‘ጆብ ፌር ኤክስፖ’ ለመጀመሪያ ጊዜ አዘጋጅቷል።

የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ጄሉ ኡመር በኤክስፖው መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት፤ ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በማበረታታት፣ የተቀናጀ ሰፊ የአቅም ግንባታ ስልጠና፣ የተሞክሮ ልውውጥና ሌሎች ስራዎችን በማከናወን የተማሪዎችን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ  እየተሰራ ይገኛል።

ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ለስራ የሚያበቃቸውን ክህሎትና አስተሳሰብ ማጎልበትና ገበያ ላይ ተፈላጊና ውጤታማ እንዲሆኑ ማስቻል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማሻሻያ ርምጃዎች መካከል አንዱ እንደሆነ አስታውሰዋል።

ይህንን አላማ ለማሳካት ዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች የሙያ ማበልጸጊያ ማዕከል ከአንድ አመት በፊት አቋቁሞ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው፤ ማዕከሉ ተማሪዎች በትምህርት ቆይታቸው ለስራ አለም ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚያስችል ሙያዊ፣ የሞራል ስብዕና፣ በራስ የመተማመን፣ የተግባቦት፣ የስራ ፈጠራና ውድድር እንዲሁም ሌሎች ክህሎቶችን እንዲያዳብሩ አልሞ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው የተማሪዎቹን የስራ ዓለም ተወዳዳሪነት ክህሎት ለማሳደግ መንግስትንና የግል ድርጅቶችን ጨምሮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በዩኒቨርሲቲው የዴሊቨሮሎጂ ዳይሬክተር ዶክተር አጥናፉ ገብረመስቀል በበኩላቸው  የመማር ማስተማር ሂደቱ ጥራት ያለው የሰው ሀይል እንዲያፈራ ሰባት ስትራቴጂዎች ተግባራዊ ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

የመምህራን የማስተማር ዘዴ መገምገምና ተከታታይ የሙያ ማሻሻያ መርሃ ግብር መተግበር፣ የተማሪዎች ተከታታይ ምዘና ሁኔታ መከታተል፣ የመምህራንና የተማሪዎች ቋንቋ ማሻሻያ ስትራቴጂ መተግበር፣ የተማሪዎች የሙያ ማበልጸጊያ ማዕከል ማቋቋምና ሌሎች ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ዶክተር ጄሉ ጠቅሰዋል።

የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስር ማጠናከርና ተማሪዎች በስራ ከተሰማሩ በኋላ በተማሩበት  መስክ መሰማራታቸውን መረጃ የማሰባሰብ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች የሙያ ማበልጸጊያ ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር ካሱ ጄልቻ ለመጀመሪያ ጊዜ በተዘጋጀው የ'ጆብ ፌር ኤክስፖ' ከተለያዩ ዘርፎች የተውጣጡ 30 ድርጅቶች እንደሚሳተፉ ማረጋገጫ መስጠታቸውን ገልጸዋል።

በአጋር ድርጅቶች በኩልም ጥሪ የተደረገላቸው በርካታ ቁጥር ያላቸው ድርጅቶች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም አክለዋል።

ከድርጅቶቹ መካከልም ትምህርት ቤቶች፣ አቬሽን ኢንዱስትሪ፣ ባንክና ኢንሹራንስ፣ በግንባታና በቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች እንደሚገኙበት ተናግረዋል።

የተማሪዎች የሙያ ማበልጸጊያ ማዕከል ዋና አላማ ተመራቂ ተማሪዎች በተመረቁበት አንድ አመት ጊዜ ውስጥ በሰለጠኑበት መስክ ተቀጥረው ወይም ስራ እንዲፈጥሩ ማስቻል መሆኑንም ተናግረዋል።  

ዶክተር ካሱ እንደገለጹት፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አዲስ አበባ ዩንቨርስቲን ጨምሮ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወጪ በማድረግ መምህራንን ከውጭ አገራት እየቀጠሩ ይገኛሉ።

ይህንን ወጪ በማስቀረት ብቃት ያላቸው ተማሪዎች በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሰፊ የስራ እድል እንዲያገኙ ማዕከሉ እየሰራ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም