ባለፉት አስር ቀናት ለዝናብ መኖር አመቺ የአየር ሁኔታ ተፈጥሮ እንደነበረ ኤጀንሲው ገለጸ

323

ግንቦት 14/ 2011  በአብዛኛው የአገሪቷ አካባቢዎች ላይ የተለያየ መጠን ያለው ዝናብ መመዝገቡን የጠቆመው ኤጀንሲው ከነበረው ጠንካራ የደመና ክምችት በአንዳንድ የአገሪቷ አካባቢዎች ላይ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ተመዝግቧል፡፡

ባለፉት አስር ቀናት በትግራይ ክልል ምስራቃዊ አጋማሽ፣በመካከለኛውና ምስራቅ አማራ፣ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በደቡብ ብሔር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል፣ በአፋርና ሱማሌ ክልሎች ላይ ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ተመዝግቧል፡፡

ከባድ ዝናብ ከተመዘገበባቸው ጣቢያዎች መካከል ኮምቦልቻ፣ ዱብቲ፣ ድሬዳዋ፣ አሶሳ፣ ሻምቡ፣ ሊሙገነት፣ ጅማ፣ ኩሉምሳ፣ ሀዋሳ፣ ወራቤ፣ ተርጫ፣ ምዕራብ አባያ፣ ደሎ መና ፣ አቦምሳና ደብረሲና ተጠቃሽ ናቸው፡፡

እንዲሁም ዲክሲ፣ አይሻ፣ ሞጣ፣ ቴፒ፣ ቡርጂ፣ ጎዴ፣ ቡሌሆራ፣ቦሬ፣፣ ማጂ፣ ሀገረማርያም፣ አየሁ፣ ጨፋ፣ ደምቢዶሎ፣ ጅግጅጋ፣ ጎዴ፣ ማሻ፣ ነገሌ እና ሴሩ ይገኙበታል፡፡

በሚቀጥሉት አስራ አንድ ቀናት ዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ሰፊ ቦታዎችን ያካተተና የተጠናከረ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል ይጠበቃል።

በተለይ ከኦሮሚያ ክልል ምሥራቅና ምዕራብ ወለጋ፣ ጅማ፣ ኢሉ አባቦራ፣ የሸዋ ዞኖች፣ ምዕራብና ምሥራቅ ሐረርጌ፣ አርሲና ባሌ፣ የጉጂና የቦረና ዞኖች፣ ድሬዳዋና ሐረር እና አዲስ አበባ በአብዛኛው ከመደበኛው ጋር የተቀራረበና አልፎ አልፎ በጥቂት ቦታዎች ላይ ከመደበኛ በላይ ዝናብ ይኖራቸዋል፡፡

እንዲሁም ከአማራ ክልል ምዕራብና ምሥራቅ ጎጃም፣ የሰሜንና የደቡብ ጎንደር ዞኖች፣ የባህርዳር ዙሪያ፣ አዊ ዞን፣ ዋግህምራ፣ የደቡብና የሰሜን ወሎ ዞኖች፣ ትግራይ ክልል የምሥራቅና የመካከለኛው ዞኖች፣ የጋምቤላና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ዞኖች፣ የደቡብ ብሔር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ዞኖች በተመሳሳይ ዝናብ የሚጥልባቸው አካባቢዎች ይኖራቸዋል።

በተጨማሪም ከሚጠናከሩ የደመና ክምችቶች በአንዳንድ ሥፍራዎች ላይ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ሊከሰት እንደሚችልም ኤጀንሲው ጠቁሟል።

በአንጻሩ ከሶማሌ ክልል ጅግጅጋ፣ ሲቲ፣ ጎዴ፣ ደጋሃቡር፣ ከአፋር ክልል ዞን 3 እና 5 ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ይጠበቃል፡፡

የሚገኘው ዝናብና እርጥበትም በተለይም ለእርሻና ግጦሽ ሳር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው የጠቆመው ኤጀንሲው አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ በተገቢው ግልጋሎት ማዋል እንዳለበት አሳስቧል።

የተቀሩት የአገሪቷ አካባቢዎች ደረቃማሆነው እንደሚሰነብቱም ኤጀንሲው ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመልክቷል።