በብራሰልስ የተከናወነው የአውሮፓ ህብረትና ኢትዮጵያ የቢዝነስ ፎረም በስኬት ተጠናቀቀ

48

አዲስ አበባ ግንቦት 14/ 2011 በአውሮፓ ህብረትና በኢትዮጵያ መካከል የተከናወነው የንግድ ፎረም በስኬት መጠናቀቁ ተገለጸ።

ጉባኤው ባሳለፍነው ሳምንት ለሁለት ቀናት በብራሰልስ ከ 200 በላይ ኢትዮጵያዊያን ፣የአውሮፓ ባለሃብቶችና የንግድ ሰዎች በተገኙበት መከናወኑን ብራሰልስ ኤክስፕረስ በድረ ገጹ ዘግቧል።

በመድረኩ የተገኙት የአውሮፓ ባለሃብቶችና የንግድ ሰዎች ከኢትዮጵያ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ጋር በአገሪቷ ባሉት የንግድ አማራጮችና በጋራ ለመስራት በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ መምከራቸውም ተገልጿል።

የጉባኤው ዓላማ የአውሮፓ የግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት በኢትዮጵያ ያለውን ተጨባጭ የንግድ አተገባበር መረጃ በማግኘት በአገሪቷ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ማስቻል ነው።

ጉባኤው በኢትዮጵያ ባለው የንግድ አማራጭ የተሳቡ ብዙ የአውሮፓ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ እንቅስቃሴ በጀመሩበት ወቅት ላይ መደረጉም አስፈላጊነቱን አጉልቶታል ተብሏል።

በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ በስራ ላይ የተሰማሩ ግዙፍ የአውሮፓ ኩባንያዎች ልምዳቸውን ለመድረኩ ተሳታፊዎች አካፍለዋል።

በመድረኩ የተሳተፉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ማርቆስ ተክሌ መንግስት በኢትዮጵያ የንግዱን ስራ በተሻለ ሁኔታ ለማሳለጥ የሚያሰችል አዲስ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ይህንኑ እንዲከታተል ያቋቋሙት ስተሪንግ ኮሚቴ ውጤታማ ስኬት ለማስመዝገብ ጠንክሮ እየሰራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አበበ አበባየሁ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግሰትና የሚመለከታቸው ድርጅቶችና ባለሃብቶች የሚገጥማቸውን ችግር ለመፍታት በትጋት እየሰሩ መሆናቸውን ለተሳታፊዎቹ ጠቁመዋል።

በአገሪቷ ባለፉት 12 ወራት አዲስ አይነት ለውጥና መሻሻሎች እየታዩ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል።

የዩኒሊቨር አፍሪካ የንግድ ጉዳዮች ዳይሬክተር ሚስተር ዶጊ ብሬው በኢትዮጵያ ያለውን እምቅ የገበያ ሁኔታ በመግለጽ ባለሃብቶች በአገሪቷ ኢንቨሰትመንት ላይ ቢሳተፉ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ጠቅሰዋል።

በተለይ በአገሪቷ እያደገ የመጣው መካከለኛ ገቢ ያለው ህብረተሰብ የአገር ውስጥ ምርት ተጠቃሚነቱን አሳድጎታልም ብለዋል።

የቮልስ ዋገን የደቡብ አፍሪካ ቀጠና ተጠሪ ቶማስ ሻፈርም ተቋማቸውን ወደ ኢትዮጵያ የሳበው በአገሪቷ ያለው የፖለቲካ ቁርጠኝነትና የመንግስት ራዕይ መሆኑን ተናግረዋል።

ባለሃብቶችም የቀደመ አመለካከታቸውን በመቀየር በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን ቢያፈሱ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።።

በጉባኤው ሁለተኛ ቀን ውሎ ተሳታፊዎቹ የሁለትዮሽ ምክክር ከማድረግ ባለፈ በጋራ ንግድ ማከናወን በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይም መምከራቸው ተገልጿል።

የጉባኤው ተሳታፊዎችም ባገኙት መረጃ በእጅጉ መርካታቸውን በመግለጽ ተመሳሳይ ጉባኤዎች በቀጣይ መከናወን እንዳለባቸው ማሳሰባቸውን ድረ ገጹ ጠቅሷል።

የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ የንግድ ፎረም ማከናወን የጀመረው እ.አ.አ ከ 2012 አንስቶ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም