በፍቼ በ209ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የተገነባው የውሃ ፕሮጀክት አገልግሎት ጀመረ

195

ፍቼ ግንቦት 12/ 2011 በፍቼ ከተማ በ209ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የተገነባው የውሃ ፕሮጀክት አገልግሎት ጀመሩን የከተማው መጠጥ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ድርጅት  አስታወቀ ፡፡
የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ አዱኛ ቶልቻ ለኢዜአ እንደገለጹት ከተማዋን ለሚቀጥሉት 25 ዓመታት ያገለግላል ተብሎ የታመነበት ፕሮጀክት ለ105 ሺህ ሕዝብ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ለማቅረብ ያስችላል።

በፕሮጀከቱ 200  ሜትር ጥልቀት ያላቸው የስምንት ጥልቅ ጉድጓዶች የተቆፈሩ ሲሆን፤ በሰከንድ 80 ሊትር ውሃ  እንደሚያመነጩ ተናግረዋል ።

የውሃ ጉድጓዶቹ  የ25ነጥብ 8ኪሎ ሜትር ቧንቧ መሥመር ከመዘርጋቱም በላይ፤ ጉድጓዶቹ የተፋጠነ አገልግሎት እንዲሰጡ የትራንስፎርመርና ጀኔሬተር ተከላ መከናወቸውን አቶ አዱኛ ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም  3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሊትር ውሃ ማጠራቀም የሚችሉ ሦስት ጋኖች ፣የሁለት የውሃ ማቀባበያ ጣቢያዎች በፕሮጀክቱ መካተታቸውን አመልክተዋል፡፡

የቀበሌ ዐ4 ነዋሪዋወይዘሮ ኑሪያ ኡስማን ፕሮጀክቱ የረጅም ዓመታት የንፁህ መጠጥ ውሃ እጦት  እንዳስቀረላቸው ገልጸዋል።

አቶ ጌታቸው ወርቁ  የተባሉ የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ ፕሮጀክቱ  ገንዘብና ጉልበት ከፍለው ከርቀት የሚያገኙትን ውሃ በደጃቸው ለማግኘት እንዳያስቻላቸው ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ  አገልግሎት መስጠት የጀመረው ከሰባት ዓመታት መጓተት በኋላ መሆኑም ታውቋል።