በግብርናው ዘርፍ ላይ ያተኮረ አገራዊ የንቅናቄ መድረክ ሊካሄድ ነው

285

ግንቦት 14/2011 በግብርናው ዘርፍ ላይ ያተኮረ አገራዊ የንቅናቄ መድረክ ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች በተገኙበት ይካሄዳል።
መድረኩ ከግንቦት 17 እስከ 18 ቀን 2011 ዓ.ም በአዳማ ከተማ የሚካሄድ ሲሆን ከወረዳ ጀምሮ የፌዴራልና የክልል አመራሮች በመድረኩ ላይ ይመክራሉ ተብሏል።

የግብርና ሚኒስስቴር የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ካሳሁን ማለቶ ለኢዜአ እንደገለጹት መድረኩ በግብርናው ዘርፍ ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ጹህፎችና ሪፖርቶች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል።

“ለግብርና ትራንስፎርሜሽን የአመራሩ ሚና” በሚል መሪሃሳብ በሚካሄደው መድረክ በኢትዮጵያ ፈጣን የግብርና ትራንስፎርሜሽን ለማምጣት የሚያስችሉ አቅጣጫዎች ይቀመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ እንደ ኤሮፓውያን አቆጣጠር በ2025 መካካለኛ ገቢ ካላቸው የዓለም አገራት ተርታ ለመሰለፍ የልማት ፖሊሲና እስትራቴጂ በመንደፍ የተለያዩ ፕሮግራሞችን እየተገበረች ትገኛለች።

ይሁን እንጂ እድገቱ የሚፈልገውን ያህል ባለመሆኑ የግብርና መዋቅራዊ ሽግግር ማረጋገጥ አልተቻለም።

ግብርናን በማዘመን ፈጣን መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችን የመሪነት ሚና ማሳደግ አስፈላጊ በመሆኑ በዚህ መድረክ ችግሮችን በመለየት ምክክር ይደረግባቸዋል ተብሏል።