ቻይና ስራ ባቆሙ 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖቿ ቦይንግ ኩባንያን ካሳ ጠየቀች

97

ግንቦት 14/2011 የቻይና አየር መንገድ ስራ ላቆሙ 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖች ካሳ እንደሚፈልግ ማስታወቁን ዥንዋን ዋቢ በማድረግ ዩናይትድ ፕሬስ ኢንተርናሽናል በድረ ገፅ ዘገባው አመልክቷል።

የምስራቅ ቻይና አየር መንገድ ስራ ባቆሙ 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖች ካሳ ይገባኛል ሲል የቻይና መንግስታዊ የመገናኛ ብዙሃን ዥንዋ ሪፖርት ያሳያል፡፡

የቻይና ምስራቃዊ አየር መንገድ እነዚህ ስራ ያቆሙ 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖች ለኪሳራ ስለዳረጉኝ ካሳ ይገባኛል ሲል መግለፁን ነው ዘገባው ያመለከተው፡፡

አየር መንገዱ ለቦይንግ ኩባንያ ስለ አጠቃላይ ካሳ ክፍያው የጠቀሰው  ዝርዝር ጉዳይ እንደሌለም በዘገባው ተጠቅሷል።

መቀመጫውን ሻንጋይ ያደረገው የምስራቃዊ ቻይና አየር መንገድ ካለፈው መጋቢት አንስቶ 14 የሚደርሱ 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖች ስራ ያቆሙት፤ በተጠቀሰው ወር ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን እንዲሁም የኢንዶኖዢያው ላየን አውሮፕላን ባጋጠማቸው አደጋ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተሳፋሪዎች ህይወት ካለፈ በኋላ ነው፡፡

ቦይንግ ኩባንያ ለፓይለቶች አስቸጋሪ የሆኑ የአውሮፕላኑ ክፍሎች ላይ የሶፍትዌር ማሻሻያ በማድረግ ላይ እንደሆነ እየተናገረ ይገኛል፡፡

በአለም ዙሪያ ያሉ አየር መንገዶችና የአቬዬሽን ኤጀንሲዎች የቦይንግ ኩባንያ ስለ 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖቹ ማሻሻያ ግልፅነት እስካልፈጠረ ድረስ አውሮፕላኖቹ ከበረራ ውጪ መሆናቸው ይቀጥላል ማለታቸውን ዩፒአይ አስታውሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም