የአብሮነት እሴቶቻችንን በማጎልበት አንድነታችንን ማጠናከር ይገባል----ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ

162

ሀዋሳ ግንቦት 13 /2011 "ኢትዮጵያውያን የአብሮነት ባህላዊ እሴቶቻችንን በማጎልበት አንድነታችንን ልናጠናክር ይገባል" ሲሉ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋየ አስታወቁ።

የዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ ለሁለት ቀን ያካሄደውን የባህል ሲምፖዚየም ተጠናቋል።

በሲምፖዚየሙ ማጠናቀቂያ ስነ ስርዓት ላይ የተገኙትየሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንደተናገሩት የአብሮነትና የጋራ እሴቶቻችንን ተጠቅመን አለመግባባቶችን በመፍታት አንድነትን ማጠናከር ይገባል ።

"በአለም አቀፍ ደረጃ እየመጡ ያሉ ለውጦች በሀገራችንም እየተስተዋሉ ነው" ያሉት ዶክተር ኤርጎጌ አብሮነትና የእርስ በርስ ትስስርን ሊሸረሽሩ የሚችሉ መጤ ባህሎችን እንዳለ ተቀብሎ መጠቀም ተገቢ እንዳልሆነ ጠቁመዋል ።

የህብረተሰቡ አንድነትና አብሮነት የተገነባው በሀገር በቀል እውቀቶች ላይ መሆኑን  የገለፁት ሚኒስትሯ "የማህበረሰቡን ስብዕና በመልካም የሚገነቡና  ትስስሩን  ሊያጠናክሩ የሚችሉ  ሀገራዊ እሴቶችን ችላ ማለት አይገባንም” ብለዋል።

የዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሀብታሙ አበበ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከሰማንያ በላይ ብሔር ብሔረሰቦች በአንድ ላይ የሚኖሩባት እንደመሆኗ ህዘቦቿ ችግሮቻቸውን በጋራ  የሚፈቱባቸውን ባህላዊ እሴቶች ማጎልበት እንደሚገባ አመላክተዋል ።

አብረው የሚኖሩ ብሄር ብሄረሰቦች በሀዘንና በደስታ የሚረዳዱበት፣ ግጭት ለመፍታትና ሰላም ለማውረድ የሚጠቀሙባቸው በርካታ ባህላዊ ክዋኔዎችና እውቀቶች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል ።

እንደ ዶክተር ሀብታሙ ገለጻ ሀገር በቀል ልምዶችና ዕውቀቶችን በማጎልበትና በማሳደግ አብሮነትን ለማጠናከር በትኩረት ሊሰራ ይገባል ።

"የሚያስተሳስሩንና አንድ የሚያደርጉን እሴቶቻችንን በመጠቀም ላይ ክፍተቶች አሉ" ያሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምርና ተቋም ተመራማሪና መምህር ዶክተር ደሳለኝ አምሳሉ ናቸው። ።

ለሰላም ግንባታ የሚያገለግሉ ሀገራዊ ጠቀሜታ ያላቸው ባህላዊ እሴቶች በአብዛኛው በግለሰቦችና በቤተሰብ ደረጃ የሚፈጠሩ ግጭቶችን ከመፍታት ባለፈ ጥቅም ላይ እየዋሉ አለመሆኑን ተናግረዋል ።

ዶክተር ደሳለኝ እንዳሉት ሀገራዊ ጠቀሜታ ላላቸው ባህላዊ እሴቶች የህግ ማዕቀፍ እንዲኖራቸው በማድረግ ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል ።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፖሊሲና ምርምር ተቋም ተመራማሪና መምህር ረዳት ፕሮፌሰር መልሰው ደጀኔ በበኩላቸው "ሀገር በቀል እውቀቶች ሀገሪቱ አሁን ላይ እያጋጠሟት ያሉ ችግሮችን በመቋቋም እንደ ሀገር እንድትቀጥል የጎላ አስተዋጻ አድርገዋል" ብለዋል ።

"ቀደምት አባቶቻችን በተለያዩ ማህበራዊ እሴቶች የተሳሰሩ ነበሩ" ያሉት ደግሞ የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህር ምህረትአብ አብርሀም ናቸው ።

"ዛሬ እነዚህ እሴቶች እየተሸረሸሩና እየጠፉ በመምጣታቸው ምክንያት የነበረን አብሮነትና በፍቅርና በጋራ ተቻችሎ የመኖር ልምድ እየጠፋ ነው" ብለዋል ።

መምህር ምህረተአብ እንዳሉት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ባህላዊ አሴቶችን ጠብቆ በማቆየት ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችሉ ጥናትና ምርምሮች ላይ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም