የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የጃፓን 'ስፕሪንግ ኢምፔሪያል' ሽልማት ሊሸለሙ ነው

63

አዲስ አበባ ግንቦት 13/2011 የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ የ2019 የጃፓን 'ስፕሪንግ ኢምፔሪያል' ሽልማት ሊሸለሙ መሆኑን በኢትዮጵያ የጃፓን ኤምባሲ አስታወቀ።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ሽልማቱ የሚሰጣቸው ለኢትዮጵያና ጃፓን የሁለትዮሽ ግንኙነት መጠናከርና በቶኪዮ ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የልማት ትብብር ጉባዔ (ቲካድ) አማካኝነት ጃፓን በአፍሪካ የምታከናውነውን የዲፕሎማሲ ስራ በማስተዋወቅ ባበረከቱት አስተዋጽኦ እንደሆነ በኢትዮጵያ የጃፓን ኤምባሲ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ሽልማቱ "Grand Cordon of The Order of The Rising Sun" የሚል ስያሜ ያለው ሲሆን ጃፓናዊ ላልሆኑና መሰል አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሰዎች የሚሰጥ  ነው።

 የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግስታት (ኢጋድ) ሊቀመንበር ሆነው እንዲሁም ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ሆና ጃፓን በደቡብ ሱዳን መረጋጋት እንዲሰፍን ላደረገችው ጥረት ድጋፍ ማድረጋቸው ለሽልማታቸው አስተዋጽኦ ማድረጉም በመግለጫው ተጠቅሷል።

ጃፓን በአፍሪካ ላሉ የሰላም አስከባሪ ሃይሎች እና ለኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ማሰልጠኛ ማዕከል የምታደርገው ድጋፍ እንዲጠናከር እንዳደረጉም ተገልጿል።

ተከታታይ የጃፓንና የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ የምክክር መድረኮችን በሰብሳቢነት በመምራት፣ የካይዘን ፍልስፍናን ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ እና የጃፓን የግሉ ዘርፍ መዋዕለ ንዋይ በኢትዮጵያ እንዲፈስ የማስተዋወቅ ስራ መስራታቸውም ተጠቁሟል።

እ.አ.አ በ2013 ከጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ጋር በመሆን በጋራ በመሩት የአምስተኛው ቶኪዮ ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የልማት የትብብር ጉባዔ (ቲካድ) የተፈጥሮ አደጋዎችን መቀነስ እና ከመከሰቱ በፊት አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግን አስመልክቶ የተዘጋጀው የዮካሃማ ድንጋጌ እና የዮካሃማ የድርጊት መርሃ ግብር እንዲጸድቅ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውም በመግለጫው ተመልክቷል።

በቶኪዮ ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የልማት ትብብር ጉባዔ (ቲካድ) አማካኝነት የአፍሪካና የጃፓን የግሉ ዘርፍ ባለሀብቶች ውይይት በማድረግ ግንኙነታቸው እንዲጠናከር የማስተዋወቅ ስራ መስራታቸውም ተጠቅሷል።

አቶ ሃይለማርያም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅትም እ.አ.አ በ2011 በጃፓን በደረሰው ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥና የሱናሚ አደጋ ለተጎጂዎች የሰማቸውን ሀዘን በመግለጽ ከኢትዮጵያ ህዝብ የተበረከተውን እርዳታ በወቅቱ ለጃፓን ማበርከታቸውም ኤምባሲው አውስቷል።

እ.አ.አ በ2011 በጃፓን ባደረጉት ይፋዊ የስራ ጉብኝትም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የጃፓን የግሉ ዘርፍ ባለሀብቶች  በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ የሚያበረታታ ውይይት በማድረግ መልካም አስተዋጽኦ እንዳበረከቱም መግለጫው አትቷል።

ጃፓን በሰኔ ወር 2011 ዓ.ም አቶ ንዋይ ገብረአብን፤ በጥቅምት ወር 2011 ዓ.ም ዶክተር አርከበ እቁባይን ለኢትዮጵያና ጃፓን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር "Order of the Rising Sun, Gold and Silver Star" የሚል ስያሜ ያለውን የክብር ሜዳሊያ መሸለሟ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም