የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን የውጭ ፖሊሲ ጉዳዮች ኃላፊ በአፍሪካ ቀንድ ጉበኝት እያደረጉ ነው

64

አዲስ አበባ ግንቦት 13/2011የአውሮፓ ሕብረት ኮሚሽን የውጭ ፖሊሲ ጉዳዮች ኃላፊና የኮሚሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት ፍሬድሪካ ሞግሔረኒ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ቀንድ የሶሰት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት እያደረጉ ነው። 

ትናንት ግንቦት 12 ቀን 2011 ጉብኝታቸውን በሶማሊያ የጀመሩት ሞግሄረኒ፤ ከሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃሰን አሊ ካይሪ ተገናኝተዋል።

በአገሪቱ የሚገኘውን የህብረቱ የስልጠና ማዕከልንም መጎብኘታቸው ተጠቁሟል።

ቀጥለውም ወደኬንያ በማቅናት ከአገሪቱ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ ከሲቪል ማህበራትና ወጣቶች ጋር እንደሚገናኙና በአገሪቱ የአውሮፓ ህብረት ልዑክ መስሪያ ቤትን መርቀው ይከፍታሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከኬንያ ጉብኝታቸው በኋላ በጂቡቲ ቆይታቸው ከአገሪቱ ፕሬዝዳንት ኡመር ሀሰን ጊሌ እና ከምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የስራ ኃላፊዎች ጋር ተገናኝተው፤ በመጨረሻም ወደ ኢትዮጵያ እንደሚዘልቁ ተገልጿል።

በአዲስ አበባ ቆይታቸውም ስለቀጣዩ የአውሮፓና የአፍሪካ ህብረት የሚኒስትሮች ስብሰባና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ጋር እንደሚወያዩ ታውቋል።

የአውሮፓ ህብረት በአየር ንብረት ለውጥ፣ በኢንቨስትመንት፣ በስደተኞች ስራ ፈጠራ መስኮች ከቀንዱ አገራት ጋር አጋርነቱን ለማጠናከር እየሰራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም