በሻሸመኔ እጽዋት አጸድ ከ2ሺህ በላይ እጽዋትን የማንበር ስራ እየተከናወነ ነው

223

ግንቦት 13/2011 በኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት የሻሸመኔ እፅዋት አፀድ ከ2ሺህ በላይ ሀገር በቀል እፅዋትን ከመመናመንና ከመጥፋት ለመጠበቅ አቅዶ በግቢው ውስጥ የማንበር(የመጠበቅ) ስራ እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ ። 

ኢንስቲትዩቱ ኢትዮጵያ ካላት 600 ብርቅዬ እፅዋቶች መካከል 400 የሚሆኑትን በሻሸመኔ እፅዋት አፀድ ለማንበር(ለመጠበቅ) እየሰራ መሆኑንም ገልጿል።

የሻሸመኔ እፅዋት አፀድ ሃላፊ አቶ ግርማ መዘምር ለኢዜአ እንደገለፁት ኢንስቲትዩቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ ካሉት ሁለት የእፅዋት አፀዶች መካከል አንዱ የሻሸመኔው ሲሆን ሁለተኛው በጅማ የሚገኝ ነው ።

የሻሸመኔ እፅዋት አፀድ በሀገር አቀፍ ደረጃ በመመናመንና በመጥፋት ላይ ያሉ ሀገር በቀልና ብርቅዬ የእፅዋት ዝርያዎችን ለመጠበቅ በ17 ሔክታር መሬት ላይ የማንበር ስራ ከጀመረ አራት ዓመት ሆኖታል ።

“እስከ አሁን ድረስ ከመላው ሀገሪቱ በጥናት ላይ ተመስርቶ በባለሙያዎች የተሰበሰቡ ከ200 በላይ እፅዋትን በሻሸመኔ የማንበር ስራ ተከናውኗል”ብለዋል ።

ከመላው ሃገሪቱ የተሰበሰቡት እጽዋትም የተቀመጡት የመድኃኒት እጽዋት፣መዓዛማ እጽዋት፣ሃገር በቀል እጽዋት በመሳሰሉት በዘጠኝ መደቦች በመለየት ነው፡፡

አፀዱ በስሩ ሁለት የጅን ባንኮች ጭምር አቅፎ የያዘ ሲሆን የወንዶ ገነት የጅን ባንክ በ4 ሔክታር መሬት ላይ 127 የመድሃኒት እፅዋትን የያዘ ነው ።

አርሲ ውስጥ ሊዺስ በተባለው የጅን ባንክ ደግሞ በ17 ሔክታር መሬት ላይ 62 ዓይነት የሀገር በቀል የደን ዝርያዎችን ማስቀመጥ እንደተቻለ ከአፀዱ ሃላፊ ገለፃ ለማወቅ ተችሏል ።

በእፅዋት አፀዱ ባዮሎጂስትና ረዳት ተመራማሪ አቶ ሂርዾ አብዲሮ እንዳሉት ከሆነ ኢትዮጵያ ከ6 ሺህ 500 እስከ 7ሺህ የሚደርሱ ሀገር በቀል የእፅዋት ዝርያዎች አሏት ።

የሻሸመኔው አፀድ በሚቀጥሉት 5 ዓመታት ከ2 ሺህ በላይ የእፅዋት ዝርያዎችን ለማንበር እንደሚረባረብ ተመራማሪው ተናግረዋል ።

በሀገራችን ከሚገኙ 600 ብርቅዬ የእፅዋት ዝርያዎች መካከል 400 የሚሆኑትን በሻሸመኔ ለማንበር መታቀዱንም አቶ ሂርጳ አስረድተዋል ።

በሻሸመኔ የእፅዋት አፀድ የእጽዋት ሳይንስ ተመራማሪ ወጣት ጃዋር ዘመዴ በበኩሉ “የእጽዋት አፀዱ ኢትዮጵያ በ2024 ዓ.ም.በዓለም አቀፍ ደረጃ የብዝሃ ህይወት ማዕከል መሆኗን ለማረጋገጥ ይሰራል” ብሏል ።

የሻሸመኔ እፅዋት አፀድ ሀገር በቀልና ብርቅዬ የእፅዋት ዝሪያዎችን ከመመናመንና ከመጥፋት ከመታደግ ባሻገር በዘርፉ ጥናትና ምርምሮችን የማካሔድ ፣ለህዝብ ክፍት በማድረግ የእውቀት ሽግግር መድረክና የመዝናኛ ማዕከል ጭምር ሆኖ እንደሚያገለግል ከአፀዱ ሃለፊ ገለፃ ለማወቅ ተችሏል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም