ዋ! ሰደድ አለ - ኢዜአ አማርኛ
ዋ! ሰደድ አለ

ገብረህይወት ካህሳይ /ኢዜአ/
በአገራችን የስምጥ ሸሎቆአካባቢዎች ሃይለኛ እሳተ ገሞራ መኖሩን የዘርፉ ተመራማሪዎች ይናገራሉ። ይህ ተፈጥሮአዊ ንዳድ በራሷ በተፈጥሮ ሚዛን ተጠብቆ ዘመናትን ያስቆጠረ ቢሆንም የእሳቱን መለኮሻ ክብሪትና ላይተር በእጃችን ይዘን እኛው ልናቀጣጥለው ተቃርበናል።
እሳተ ጎሞራው ከፈነዳ ደግሞ ፍጥረታት በሙሉ ይጠፋሉ። በተለይ ሰብአዊ ፍጡር አጥፍቶ ጠፊ ሆኖ በገዛ እጁ ህልውናውን ያጣል። በሰፈሩት ቁና….እንዲሉ መልሶ እኛውኑ ይፈጀናል።
ዶክተር ለማ አበራ በኦሮሚያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የባቱ ዓሳና ሌሎች የውሃ ውስጥ ህይወት ምርምር ማእከል ስራ አስኪያጅና ከፍተኛ ተመራማሪ ናቸው ። በአገራችን የስምጥ ሸሎቆ አካባቢ ሃይለኛ እሳተ ጎሞራ መኖሩን በዘርፉ ከፍተኛ ባለሙያዎች ተረጋግጧል ባይ ናቸው ።
ታዲያ ! እሳተ ጎሞራው አቀዝቅዘው የያዙት በስምጥ ሸሎቆ አካባቢ የሚገኙ የዝዋይ፣ የአቢጃታና ሻላ የመሳሰሉ ሐይቆችና ሌሎች የውሃ አማራጮች እንደሆኑ ዶክተር ለማ ይናገራሉ።
አሁን ግን በእነዚህ ሐይቆችና የውሃ አማራጮች ላይ ያንዣበበው የመድረቅና ጭራሹኑ የመጥፋት አደጋ እሳተ ጎሞራው ሊፈነዳ የሚችልበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት መኖሩን ጠቁመዋል።
እንደ ከፍተኛ ተመራማሪው ገለፃ የዝዋይ ሀይቅ ከአራት ዓመታት በፊት በዓመት በአማካይ ከ4 ሺህ 500 እስከ 6ሺህ ቶን የሚደርስ ዓሳ ይመረትበት ነበር ። አሁን ግን የሐይቁ የዓሳ ምርት ከ1ሺህ ቶንም ያነሰ ነው።
የሐይቁ ውሃ ጥልቀቱም ቢሆን ከ12 ሜትር ወደ 4 ሜትርና ከዚያ በታች መውረዱን ያስረዳሉ።
ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ በዝዋይ ሐይቅ መታየት የጀመረው የእምቦጭ አረም የብክለት ምልክት ነው ባይ ናቸው። በሐይቁ ዙሪያ በብዛት የሚገኙ በመስኖ አትክልትና ፍራፍሬ አልሚዎች፣ ትላልቅ የአበባ ልማት ድርጅቶች፣ ህገወጥ ዓሳ አጥማጆችና የሞጆ ሀዋሳ የፍጥነት መንገድ ከአቅሙ በላይ ጫና በማሳደር አደጋ ላይ ጥለውታል።
በተለይ የሞጆ ሀዋሳ የፍጥነት መንገድ ፕሮጀክት ቀኑን ሙሉ አቧራ ለመከላከል ሲባል በቦቴዎች ከሐይቁ ውሃ እየቀዳ በመንገዱ ላይ በማፍሰስ ተጨማሪ ጫና እያሳደረ ነው ሲሉ ተመራማሪው ቅሬታ አሰምተዋል።
ከአርሲ ከታርና ከጉራጌ መቂ ወንዞች ወደ ዝዋይ ሃይቅ ይገባ የነበረው ንፁህ ውሃ በየአካባቢው በሚካሄዱ የመስኖ ልማቶች ተቆራርጠው እየቀሩ መሆናቸው ደግሞ ለሃይቁ ብክለትም ሆነ ለውሃ መጠኑ መቀነስ አሉታዊ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ዶክተር ለማ አስረድተዋል።
ከፍተኛ ተመራማሪው የዝዋይ ሀይቅን አስመልክተው የሰነዘሩት ሓሳብ በከፋ መልኩ በአብጃታ ሃይቅም እየታየ ነው የሚሉት ደግሞ የአብጃታና ሻላ ሀይቆች ብሄራዊ ፓርክ ሃላፊ አቶ ባንኪ ቡደሞ ናቸው።
የአብጃታ ሀይቅ ከአሁን በፊት 194 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት የነበረው ሲሆን በአሁን ጊዜ ከግማሽ በላይ በመቀነስ ከ80 ስኩዌር ኪሎ ሜትር በታች ወደ መሆን ወርዷል።
የሃይቁ ጥልቀትም ቢሆን በአስደንጋጭ ሁኔታ ከ14 ሜትር ወደ 2 ሜትር ዝቅ ማለቱን ሃላፊው ገልፀው በዚሁ ከቀጠለ በሚቀጥሉት አምስትና ስድስት ዓመታት ሙሉ በሙሉ ደርቆ ልናጣው እንችላለን ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል።
በነገራችን ላይ የአብጃታና ሻላ ሀይቆች ስደተኛ የአውሮፓ ወፎችን ጨምሮ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙትን ፍላሚንጎና ፔሊካን የመሳሰሉት 463 የአእዋፍ ዝሪያዎች መኖሪያ ነው።
አእዋፋቱ የአብጃታ ሀይቅን የሚመገቡበት የሻላ ሀይቅ ደግሞ የሚራቡበት ቦታ ነው።
በርካታ የኤሲያና የአውሮፓ አእዋፋት ከመስከረም እስከ ህዳር ባሉት የብርድ ወራት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በአብጃታና ሻላ ሐይቆች ቆይታ የሚያደርጉበት ቦታ መሆኑንም ሃላፊው ያስረዳሉ።
ለአብጃታ ሐይቅ እየደረቀ መምጣት ዋናው ምክንያት ወደ ሀይቁ የሚፈሱ ገባር ወንዞች በመስኖ ልማት ጫና ፍሰታቸው መቋረጡ፣ በአካባቢው የሚገኘው የሶዳ አሽ ፋብሪካ በቀጥታ በፓምፕ እየሳበ የሃይቁን ውሃ የሚጠቀም መሆኑንና የደን መመናመንን ተከትሎ ሃይቁ በደለል በመጎዳቱ ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ ፓርኩ ክልል እየገቡ መንደር መስርተው መኖር የጀመሩ የአካባቢው ሰዎች ቁጥር 6 ሺህ አባወሯዎች መድረሱን ሃላፊው ገልፀው፤ በፓርኩ ስካውቶች ህገ ወጥ ሰፈራ ለመከላከል የተደረገው ጥረት ለሁለት ሰራተኞች መሞትና ለሰባት ሰራተኞች የአካል ጉዳት ምክንያት ሆኗል።
የግጭቱ መንስኤ ደን እየጨፈጨፉ ከሰል ማክሰልና አሸዋ ማውጣት እንዲተዉ ሲነገራቸው ፈቃደኛ ሳይሆኑ በመቅረት ጥቃት ለማድረስ በመነሳታቸው እንደሆነ የፓርኩ ሃላፊ አስረድተዋል።
የሀይቆቹ ጉዳት ለወደፊቱ ሊከሰት ከሚችለው የእሳተ ጎሞራ ስጋት ባሻገር በአሁኑ ወቅት በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ቀጥተኛ ተጠቂዎች አድርጓቸዋል ።
አቶ ጋዲሳ እሬሳ የ67 ዓመት የእድሜ ባለፀጋና የዝዋይ ከተማ ነዋሪ ናቸው። ከወጣትነታቸው ጀምሮ በዓሳ ማጥመድ ስራ ማሳለፋቸውን ገልፀው "የዝዋይ ሐይቅ እንደ አሁኑ ተጎድቶና ተጎሳቁሎ አይቼው አላውቅም" ነው ያሉት።
"ያለማንም ተቆጣጣሪና ጠባቂ ማንም እየመጣ እንደ አሻው የሚጠቀምበት ሐይቅ በመሆኑ የውሃ መጠኑ እየቀነሰ፣ የዓሳ ምርቱ ደግሞ እየጠፋ በመምጣቱ ህልውናችን አደጋ ላይ ወድቋል" ሲሉ አዛውንቱ ቅሬታቸው ገልፀዋል።
የዝዋይ ባቱ ዓሳ አጥማጅ ማህበር ፀሀፊ አቶ ደራሮ ሆራ በበኩላቸው "የዝዋይ ሀይቅ ከአቅም በላይ ጫና የበዛበትና ለመጥፋት አደጋ የተጋለጠ በመሆኑ አፋጣኝ መፍትሄ የሚያስፈልገው ነው" ባይ ናቸው።
ኑሮአቸውን በዝዋይ ሀይቅ የዓሳ ምርት ላይ የተመሰረተ በ14 ማህበራት የተደራጁ በርካታ ሰዎች ሐይቁ ባጋጠመው ችግር ምክንያት የሚላስ የሚቀመስ እያጡ መምጣታቸውን አስረድተዋል።

የአርሲ ነገሌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደስታ አብዶ በበኩላቸው "የአብጃታ ሐይቅ እየደረቀ በመምጣቱ የአካባቢው ነዋሪዎች በአውሎ ንፋስና በአቧራ እየተጎዱ ነው " ብለዋል።
በሐይቆቹ እየደረሰ ያለው ሰው ሰራሽ ጉዳት ከወዲሁ መፍትሔ ካልተፈለገለት አደጋው የከፋ እንደሚሆን ግንዛቤ በመፈጠሩ የተቀናጀና የተጠናከረ ባይሆንም የመከላከል እርምጃዎች መውሰድ ተጀምሯል።
የዝዋይ ሐይቅ አሳሳቢነትን በመረዳት ከአርሲ ዩኒቨርሲቲና ከሌሎች ተቋማት ጋር በመሆን የሃይቁን ጫና ለመቀነስና መልሶ እንዲያገግም የሚያደርጉ ጥናቶችና ምክረ ሃሰቦች እየቀረቡ ናቸው።
ዶክተር ለማ እንደገለፁት ቅጥ ያጣ የሀይቅ ውሃ አጠቃቀም መልክ ለማስያዝም ጥረት መደረግ ተጀምሯል።
በአብጃታ ሐይቅ በኩል ደግሞ በመስኖ ልማት ላይ የተሰማሩ የአበባ ልማቶች ከገባር ወንዝ ይልቅ የከርሰ ምድር ውሃ አበልፅገው እንዲጠቀሙ፣ የተፈጥሮ ሀብት ልማት በስፋት እንዲከናወን፣ በፓርኩ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ደን ከመጨፍጨፍ እንዲታቀቡና በሃላፊነት መንፈስ ሃይቁን እንዲጠብቁ በማነሳሳት ወደ መፍትሄው ተገብቷል።
ለመፍትሔው ተግባራዊነት የምእራብ አርሲና የምስራቅ ሸዋ ዞኖች አስተዳዳሪዎች፣ አባገዳዎች፣ ቄሮዎችና የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ ማድረግ መጀመራቸው የፓርኩ ሃላፊ በመልካም ጎኑ አንስተዋል።
የሶዳ አሽ ፋብሪካ ከወንዙ እየሳበ የሚጠቀመውን ውሃ ማቋረጡና ሼር ኢትዮጵያ የተባለ የአበባ ልማት ድርጅት ከቡልቡላ ወንዝ የሚጠቀመው የውሃ መጠን መቀነሱ የአብጃታ ሓይቅን ለማዳን አጋዥ ሚና ይኖረዋል የሚል ተስፋ አሳድሯል።
የነገሌ አርሲ ኡታዋዩ አባገዳዎች ሰብሳቢ አባገዳ ቱፋ ደራርሱ ሐይቆቹ ከመጥፋት ይድናሉ የሚል ተስፋ አላቸው። በአካባቢው የሚገኙ አባገዳዎች በተጠናከረ መንገድ ህዝቡን በማስተባበር ብሄራዊ ፓርኩን ለመታደግ እየተረባረቡ መሆናቸውን ያስረዳሉ።
700 ወጣቶች በማደራጀትም ፓርኩን እየጠበቁና የአካባቢ ጥበቃ ስራን በማከናወን ተጠቀሚዎች እንዲሆኑ አሰማርተናቸዋል ሲሉ የአባ ገዳዎቹ ሰብሳቢ ተናግረዋል።
"የተጀመረው የተቀናጀ ጥረት ተስፋ ሰጪ በመሆኑ የመንግስት ድጋፍ ከታከለበት ብሄራዊ ፓርኩን እንደምናድነው እርግጠኛ ነኝ " ሲሉ አባገዳ ቱፋ ደራርሱ በልበ ሙሉነት ተናግረዋል።
አዎን ! በህብረተሰቡና በአካባቢው የመስተዳድር አካላት ዘንድ ሐይቆቹን ለማዳን ተስፋ ሰጪ ጥረት ተጀምሯል ። ሁሉንም የየድርሻውን ለማበርከት ግን የመንግስትን እገዛ እየጠየቀ ነው ። መንግስት በበኩሉ በርቱ አለሁላችሁ ማለትና በተግባር ማገዝ ይጠበቅበታል።
ሁላችንም ከችግር ፈጣሪነት እጃችንን በመሰብሰብ የዘላቂ መፍትሔው አካል መሆን አለብን የምንለው "ሀ"ራስን ለማዳን መሆኑን መዘንጋት የለብንም። ካልሆነ ግን የሰቆቃው ገፈት ቀማሽ እኛው እራሳችን እንሆናለን ። ለዛውም ነው ዋ ! ሰደድ አለ የምንለው።