በጭልጋ ወረዳ ወደ መኖሪያቸው የተመለሱ አርሶ አደሮች የእርሻ ሥራቸውን ለማካሄድ መቸገራቸውን ገለጹ

50

ጎንደር ግንቦት 13 / 2011 በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጭልጋ ወረዳ ተፈናቅለው ወደ መኖሪያቸው የተመለሱ አርሶ አደሮች በእርሻ መሳሪያዎችና በግብዓት እጦት የእርሻ ሥራቸውን አለመጀመራቸውን ገለጹ፡፡

የዞኑ ግብርና መምሪያ ለእርሻ መሳሪያዎችና ለምርት ግብዓቶች አቅርቦት ስድስት ሚሊዮን ብር ግዢ ተመድቧል ይላል፡፡

በወረዳው ተፈጥሮ  በነበረው ግጭት የተፈናቀሉ አርሶ አደሮች ወደ ቀድሞው መኖሪያቸው ቢመለሱም፤ የእርሻ ሥራቸውን ለማካሄድ መቸገራቸውን ለኢዜአ አስታውቀዋል።

በአካባቢው በተፈጠረው ሰላም ከአንድ ወር በፊት ወደ መኖሪያቸው የተመለሱት የላዛ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር የኔሁን በላይ በግጭቱ ቤትና ንብረታቸው በመውደሙ የእርሻ ሥራቸውን ለማከናወን ተቸግረዋል።

በአካባቢያቸው እየጣለ ያለው ዝናብ ለእርሻ ሥራ ምቹ መሆኑን አመልክተው፣ለዚህም መንግሥት ሥራችን በወቅቱ እንድናከናወን እገዛ ሊያደርግልን ይገባል ብለዋል፡፡

''የእርሻ በሬ የለኝም። ማረሻና ለዘር ብዬ በጎተራ ያስቀመጥኩት ጥሪት በሙሉ በግጭቱ ሳቢያ ተዘርፏል። የተረፈውም ተቃጥሏል'' ያሉት ደግሞ አርሶ አደር ሲሳይ መልኬ ናቸው፡፡

“እርዳታ ጠባቂ በመሆን ኑሮዬን መግፋት ምኞት የለኝም” የሚሉት አርሶ አደር ሲሳይ፣ መንግሥት የእርሻ በሬን ጨምሮ ማረሻ፣ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በማቅረብ ወቅቱ ሳያልፍ ድጋፍ እንደያደርግ ጠይቀዋል፡፡

“ላለፉት አምስት ወራት በጊዜያዊ መጠለያ በአስቸጋሪ ህይወት ውስጥ ቆይቻለሁ’’፤ ከአንድ ወር በፊት ወደ ቀዬ ብመለስም የእርሻ ስራ መጀመር አልቻልኩም ያሉት ደግሞ የምስራቅ ደንቢያ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር መልካሙ ማሩ ናቸው፡፡

መንግሥት ሰላምን በማረጋገጥ ወደ ቀድሞ መኖሪየችችን እንድንመለስ ያደረገው ጥረት መልካም ቢሆንም፤ የእርሻ ሥራቸውን ለማከናወን ትኩረት ይስጠን ብለዋል፡፡

የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አንዱአለም ሙሉ እንደተናገሩት ወደ መኖሪያቸው የተመለሱ አርሶ አደሮች ፈጥነው ወደ እርሻ ሥራ እንዲገቡ ለግብአት አቅርቦት የሚውል ስድስት ሚሊዮን ብር ተመድቧል፡፡

በበጀቱ ከ41ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር እንዲሁም  ከ79ሺህ በላይ  የእጅ የእርሻ መሳሪያዎች ተገዝተው ለስርጭት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

ስርጭቱን በዚህ ወር ሙሉ በሙሉ ተፈጻሚ ለማድረግ በክልልና በዞን ደረጃ የተቋቋመው ጥምር ግብረ ኃይል ተቀናጅቶ በመሥራት ላይ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

ግብረ ኃይሉ ተፈናቃይ አርሶአደሮች የደረሰባቸውን የንብረት ጉዳት በጥናት ለይቷል'' ያሉት ኃላፊው፣ የእርሻ በሬ የሌላቸው አርሶ አደሮች በኪራይ እንዲታረስላቸው ለማድረግ ታቅዷል ብለዋል፡፡

ከዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በዞኑ አምስት ወረዳዎች የሚገኙ ከ20ሺህ በላይ ተፈናቃይ አርሶአደሮች ወደ መኖሪያቸው ተመልሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም