የዓለም ዋንጫ በየአገራት ጉዞ ዛሬ ይጠናቃቃል

206
አዲስ አበባ ሚያዝያ 22/2010 በተለያዩ አገሮች ጉዞ ሲያደርግ የነበረው የዓለም ዋንጫ ዛሬ ፍጻሜውን ያገኛል። ሩሲያ የምታዘጋጀው 21ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ከሰኔ 7 እስከ ሐምሌ 8 ቀን 2010 ዓ.ም ይካሄዳል። የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ፌደሬሽኖች ማህበር (ፊፋ) ከውድድሩ ጅማሮ አስቀድሞ እንደሚያደርገው ሁሉ የዓለም ዋንጫው በተመረጡ አገሮች ጉዞ አድርጓል። በዚሁ መሰረት የዘንድሮው ጉዞውን ጥር 15 ቀን 2010 ዓ.ም በስሪላንካ ርዕሰ መዲና ኮሎምቦ የጀመረ ሲሆን ዛሬ በጃፓኗ ሺዞኮዋ ከተማ ያጠናቅቃል። ነገ ዋንጫው ወደ ሩሲያዋ ቭላዲቮስቶክ ከተማ የሚመለስ ይሆናል። በስድስቱ አህጉራት በሚገኙ 51 አገሮች የተዘዋወረው የዓለም ዋንጫ፣ በነዚህ አገሮች የ91 ከተሞች ደጋፊዎች ሲጎበኙት የቆየ ሲሆን በአጠቃላይ ጉዞው 126 ሺህ ኪሎ ሜትር ሸፍኗል። በተያዘለት መርሃ ግብርም ዋንጫው የካቲት 17 እና 18 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ላደረገው የሁለት ቀናት ቆይታ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በብሔራዊ ቤተ መንግስት በተካሄደ ስነ ስርአት አቀባበል እንዳደረጉለት የሚታወስ ነው። የእግር ኳስ ቤተሰቡ በግዮን ሆቴል ከዓለም ዋንጫው ጋር ፎቶ የተነሳበት መርሃ-ግብርም ተካሄዶ ነበር። በአጠቃላይ በአፍሪካ ዋንጫው በ12 ከተሞች ተዘዋውሯል። ኢትዮጵያ፣ ሴኔጋል፣ ሞዛምቢክ፣ ኬንያ፣ ግብጽ፣ ኮትዲቭዋር፣ ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካና ኡጋንዳ የዓለም ዋንጫው የዞረባቸው የአፍሪካ አገሮች ናቸው። የዓለም ዋንጫው ጉዞ የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ፌደሬሽኖች ማኅበር (ፊፋ) ከኮካ ኮላ ኩባንያ ጋር በመተባበር የሚያዘጋጀው ነው። የዓለም ዋንጫ ጉዞ የተጀመረው እ.አ.አ 2006 ጀርመን ባስተናገደችው 18ኛው የዓለም ዋንጫ ሲሆን በወቅቱ ጉዞው በ28 አገሮች የሚገኙ 31 ከተሞችን ማዳረሱ የሚታወስ ነው። በሰባቱ አህጉራት ቅርፅ የተሰየመው የዓለም ዋንጫ፣ ከ18 ካራት ወርቅ የተሠራ ሲሆን፣ ክብደቱም 6 ነጥብ 142 ኪሎ ግራም ይመዝናል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም